EthiopianReporter.com 


ዜና
የኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት ይዞታ እንዳይነጠቅ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ሰላማዊት መንገሻ

ቀን: January 10, 2024

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ልማት ድርጅት (ኢግልድ) የጅግጅጋ ቅርንጫፍ  ሕጋዊ የቦታ ይዞታን ለመንጠቅ የሚደረገውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ፣ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮስትራክሽን ቢሮ እንዲያስቆም ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይህንን ማሳሰቢያ  የሰጠው፣ ባለፈው ሳምንት በሶማሌ ክልል በተመረጡ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን ከጎበኘ በኋላ፣ በሶማሌ ክልል መንግሥት ለከተማ መሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ግብረ መልስ በሰጠበት ወቅት ነው።

‹‹ኢግልድ›› የሚለውን ስያሜ ከማግኘቱ 2006 ዓ.ም. በፊት ጅንአድ፣ ከዚያ በፊት ደግሞ ‹‹የአገር ውስጥ ማከፋፈያ›› የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚያቀርበው ድርጅቱ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ከ2,000 በላይ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባረፈ ይዞታ፣ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢግልድ ባልደረባ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢግልድ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ይዞታን መጋፋት የጀመረው በጅግጅጋ ከተማ የ03 ቀበሌ አስተዳደር ነው፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር በሕጋዊ መንገድ ይዞታውን ለመጠቅለል ጥረት እየተደረገ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢግልድ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ከገበያ ማዕከል ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ ግለሰቦች ቦታውን ራሳቸውን የንግድ ሥራ ስለሚፈልጉት በቀበሌው ላይ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ኢግልድ ኃላፊ ወ/ሮ ምሥራቅ ነጋሽ በበኩላቸው፣ ይዞታውን በተመለከተ በቀድሞው የቀበሌ ሊቀመንበር በኩል ከፍተኛ ጫና ሲደረግ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ አሁን በቅርብ ከተሾሙት የቀበሌው ሊቀመንበር ጋር ችግሩን ለመፍታት ንግግር እየተደረገ መሆኑን ወ/ሮ ምሥራቅ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ቀድሞ የነበራት የቀበሌ ሊቀመንበር ይዞታው ለኢግልድ አይገባም በማለት በተደጋጋሚ የይዞታ መጋፋት በመፍጠር፣ የግቢውን አጥር እንዲፈርስ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

የይዞታ ጥያቄውን ቀበሌው የሚያነሳበት ዋነኛ ምክንያት የኢግልድ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ የቦታ ግብር የሚከፈለው በፌዴራል በኩል እንደሆነ ገልጸው፣ ይዞታው በክልሉ የሚገኝ ሆኖ ሳለ በፌዴራል ቅርንጫፍ ክፍያ መፈጸሙ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የቦታ ግብር ክፍያ በፌዴራል የሚከፈልበት ምክንያት ኢግልድ ከፍተኛ ታክስ ከፋይ እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ በማቅረብ፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

በሶማሌ ክልል የከተማ መሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል  ኃላፊ  አቶ  ጣይብ መሐመድ፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ልማት ድርጅት የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ከይዞታ ጋር በተገናኘ የሚታየው ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ በልዩ ትኩረት የሚታይ መሆኑን በቋሚ ኮሚቴው ጉብኝት ወቅት መናገራቸው ታውቋል፡፡