
ዜና ከኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ወደ ባህር ዳር የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ዕገታና ዘረፋ እየተፈጸመብን ነው…
ቀን: January 10, 2024
ከአማራ ክልል ኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ተነስተው የተለያዩ ዕቃዎችን በመጫን ወደ ባህር ዳርና ጎንደር የሚሄዱ አሽከርካሪዎች፣ ከጋሸና ከተማ አቅራቢያ ጀምሮ እስከ ወረታ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ዕገታና ዘረፋ እየተፈጸመብን ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡
ደብረ ዘቢጥ ከሚባለው አካባቢ ጀምሮ ጎብ ጎብ፣ ክምር ድንጋይ፣ ገሰይና አመድበር የሚባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝርፊያ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን የተናገሩት አሽከርካሪዎቹ፣ ከከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኙና ጫካ የሚበዛባቸው መሆናቸውን አሽከርካሪዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ዘረፋው ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ ግን በተለየ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉትን በማገት እንግልትና ማስፈራራት እያደረሱባቸው እንደሆነ አሽከርካሪዎቹ አክለዋል፡፡
ቅዳሜ ታኅሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኮምቦልቻ ዕቃ ጭኖ ሲሄድ ዓለም ሳጋት በተባለው ቦታ በዘራፊዎች ተይዞ 70 ሺሕ ብር ከፍለው መለቀቃቸውን፣ አቶ ሀብታሙ ከበደ የተባሉ አሽከርካሪ ተናግረዋል፡፡
ዘራፊዎቹ እነማን ናቸው ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አሽከርካሪው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዘራፊዎቹ ከጫካ የሚወጡ ወንበዴዎች ናቸው፤›› ብለው፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቅርብ ርቀት ቢኖሩም ወደ ቦታው ሲሄዱ አጋቾቹ ስልክ በመደዋወል ወደ ጫካ በመግባት እንደሚሸሹ ገልጸዋል፡፡
‹‹ሁለትና ሦስት ሺሕ ብር እየከፈልን ማለፍ ለምደነው ነበር፤›› ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንዲከፍሉ እያስገደዷቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሁለት መቶ ሺሕ ብር እንድከፍል ጠይቀውኝ፣ ነገር ግን ባንክ የነበረኝን 70 ሺሕ ብር በሞባይል ባንኪንግ ከፍዬ ከሞት ተርፌያለሁ፤›› ሲሉ አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡
ገንዘብ ሳይከፍሉ ለማለፍ ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ የነበሩ ሦስት ጓደኞቻቸው ገደል በመግባት ሕይወታቸው ማለፉን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ ከዚህ በኋላ ወደ ባህር ዳር መስመር እንደማይሄዱ ገልጸዋል፡፡
አሽከርካሪው በአፋር መስመር በኩልም ተመሳሳይ ዘረፋዎችና ግድያዎች መኖራቸውን፣ በአጠቃላይ በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ግድያ፣ ዕገታና ዘረፋ ሊቆም ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በየቦታው ዘረፋ እየተባባሰ በመሆኑና ለሕይወቱ አሥጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ ሥራ ለማቆም መገደዱን የተናገረው ደግሞ አቶ ሙሐመድ ሀሰን የተባለ አሽከርካሪ ነው፡፡
‹‹ዘራፊዎቹ ሲጀምሩ ለፋኖ ድጋፍ አዋጡ በማለት›› በ20 እና በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በማስቆም የሚሰጧቸውን ገንዘብ በመቀበል እንደነበር ያስታወሰው አሽከርካሪው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ድርጊቱ ወደ ዘረፋ ተቀይሮ የተጫነ እህል ማውረድ፣ ሞባይል ስልክ መንጠቅና ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ መስፋፋቱን ገልጿል፡፡
ይህንን ማድረግ ያልቻለ አሽከርካሪ ደግሞ አግተው በመውሰድ የተሽከርካሪውን ባለቤት ገንዘብ እንደሚጠይቁ አቶ ሙሐመድ አስረድቷል፡፡
ከጋይንት እስከ ደብረ ታቦር ባለው መንገድ ሦስት የጥቁር ዓባይ አሽከርካሪዎች ታግተው እያንዳንዳቸው 80 ሺሕ ብር ከፍለው መለቀቃቸውን፣ ሌሎች ሦስት አሽከርካሪዎች መገደላቸውን በቅርብ እንደሚያውቅ አቶ ሙሐመድ ተናግሯል፡፡
‹‹ለሾፌር መቶ ሺሕ ብር ለረዳት ሃምሳ ሺሕ ብር ተመን አውጥተው እየተቀበሉ ነው፤›› ያለው ደግሞ፣ በረዳትነት ሥራ የተሰማራው ወጣት ከማል አማረ ነው፡፡
‹‹የፋኖ አባላት ነን ለተተኳሽ መግዣ አዋጡ›› በማለት፣ የአሽከርካሪና የረዳት ተመን በማውጣት ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቋቸው መሆኑን ወጣቱ ገልጿል፡፡
የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ያልቻለ እስከ ሞት ድረስ ሊፈረድበት ይችላል ሲል የችግሩን አስከፊነት ተናግሯል፡፡
ጉዳዩን በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲያመለክቱና መከላከያም ወደ ተባለው ቦታ ሲሄድ፣ ዘራፊዎቹ በአካባቢው እንደማይገኙ ወጣት ከማል ገልጿል፡፡
