EthiopianReporter.com 

ሳሙኤል ቦጋለ

January 10, 2024

የአሜሪካው አላስካ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ-9

የአሜሪካው አላስካ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ-9 (Boeing 737 Max-9) አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ አደጋ ከገጠመው በኋላ፣ በአሜሪካና በሌሎች አገሮች የሚገኙ በርካታ አየር መንገዶች አውሮፕላኑን እንዳይበር እያገዱ ነው፡፡

ከዶሬጐን ግዛት ፖርትላንድ ከተማ ተነስቶ ወደ ካሊፎርንያ ግዛት ኮንታሪዬ እየበረረ የነበረው የአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተነሳ ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ፣ የኋላ በሩ ክፍል የሆነው የሆዱ አካል በአየር ላይ ተከፍቶ መውደቁ ይታወሳል፡፡

በዚህም ምክንያት የአውሮፕላኑ ባለቤት አላስካ አየር መንገድና ሌላኛው የአሜሪካ ዩናይትድ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ አየር መንገዶች፣ ቦይንግ ኩባንያ የሠራቸውን ቦይንግ 737 ማክስ-9 አውሮፕላኖች ለተጨማሪ ምርመራ ነው እንዳይበሩ ያገዷቸው፡፡

ምንም እንኳን አደጋው በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ቢገለጽም፣ አደጋው ያጋጠመው በረራው ከተጀመረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላና የበረራው ከፍታም 16 ሺሕ ጫማ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አውሮፕላኑ መብረር በነበረበት 40 ሺሕ ጫማ ከፍታ ላይ ሆኖ ቢሆንና ተሳፋሪዎችም ቆመው ቢሆን ኖሮ በውስጡ በተሳፈሩት 174 ተሳፋሪዎችና ስድስት የበረራ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችል እንደነበር፣ የአሜሪካ ብሔራዊ ትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የደቡብ አሜሪካ አገሮች የፓናማና የሜክሲኮ ንብረት የሆኑት ኮፓ አየር መንገድና አይሮ ሜክሲኮም ያሏቸውን ከ40 የሚበልጡ ቦይንግ 737 ማክስ-9 አውሮፕላኖች ያገዱ ሲሆን፣ ተርኪሽ አየር መንገድም ያሉትን አምስት አውሮፕላኖች እንዳይበሩ አግዷቸዋል፡፡ ዩናይትድ አየር መንገድ 79 የቦይንግ 737 ማክስ-9 አውሮፕላኖች ሲኖሩት፣ አላስካ አየር መንገድ ደግሞ 65 አሉት፡፡

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በመላው ዓለም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን 171 የቦይንግ 737 ማክስ-9 አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ የነበረው አደጋው በተከሰተ ዕለት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም መሰል አውሮፕላኖች እንዳሉትና ዕገዳው ይመለከተው እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ የቦይንግ 737 ማክስ-9 አውሮፕላኖች እንደሌሉትና ከእነዚህ ምርቶች ውስጥ በማክስ-8 ብቻ እንደሚጠቀም ገልጿል፡፡

የአሜሪካው ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ዕገዳ እንደማይመለከተው፣ እንዲሁም ምንም ማድረግ እንደማይጠበቅበት ለሪፖርተር በላከው አጭር የኢሜይል መልስ አስታውቋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደርንና የቦይንግ ኩባንያን መመርያዎች ይከተላል፡፡ እስካሁን ምንም ነገር የለም፣ ነገር ግን በማክስ-8 አውሮፕላኖች ላይ የሚወጣ ትዕዛዝ ካለ እሱን ይከተላል፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን፣ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሲበር የመከስከስ አደጋ አጋጥሞት፣ ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም፡፡

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ አስቀድሞ የኢንዶኔዥያው ላይን አየር ንብረት የሆነው ተመሳሳይ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመከስከስ አደጋ ገጥሞት በውስጡ የነበሩት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ የአቪዬሽን አስተዳደርም ከኢትዮጵያ አደጋ በኋላ ለ20 ወራት ያህል ይህንን አውሮፕላን ከበረራ አግዶ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡