ለ4 ወር የምርት ሂደቱን አቋርጦ የነበረዉ ሞሐ ለስላሳ መጠጦች በድጋሚ ማምረት መጀመሩ ተነገረ
ሞሐ አዲስ ስራ አስፈፃሚ ከ30 ዓመታት በኃላ ተሹሞለታል
(ካፒታል : ጥር 01 ፤ 2016 ዓ.ም.)
ከመስከረም ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ምርት አቁሞ የነበረዉ ሞሐ ታህሳስ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ተክለሃይማኖት ከሚገኘዉ በስተቀር ጎተራና ሰሚት እንዲሁም በክልል ከተሞች በሚገኙ ፋብሪካዎቹ ተቋርጦ የነበረዉን ምርት በድጋሚ መጀመሩ ተሰምቷል።

ምርት ማቆሙ ከታወቀ ወዲህ በመጋዘን የተቀመጡና ከዚህ ቀደም የተመረቱ ለስላሳ መጠጦችን ሲያከፋፍል እንደነበር የሚናገሩት ምንጮች በአየር ትራንስፖርት ቀድመዉ በገብ ጥሬ እቃዎች ምርቱ መጀመሩን ለካፒታል ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ማምረቻ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅን ጨምሮ የአስተዳደር ሰራተኞች የፋይናንስ ባለሞያዎች እንዲሁም ድርጅቱን በቢሊዮን ብር ኪሳራ ዳርገዋል የተባሉት አመራሮች በድንገት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉና በምትኩ አዲስ አመራሮች ከሳምንት በፊት መተካታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
እንዲነሱ የተደረጉት አመራሮች “ድርጅቱ ዉስጥ በሌለ ሰዉ :- ጡረታ በወጡና በህይወት በሌሉ የቀድሞ ሰራተኞች ስም ደመወዝ ሲከፍሉ” እንደነበር ምንጮቻችን ገልፀዋል።
ድርጅቱን ከ30 ዓመት በላይ በዋና ስራ አስፈፃሚነት ሲያስተዳድሩ በነበሩት በጌታቸው ቢርቦ ምትክ ከዚህ ቀደም የአልሳም ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አማኑኤል ሙኤ በጊዜያዊነት መሾማቸው ተሰምቷል።
በሜድሮክ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ማምረቻ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት በጀማል አህመድ ከ15 ቀን በፊት በጊዜያዊነት አዲሱን ዋና ስራ አስፈፃሚ መሾማቸው ተሰምቷል።
ከኃላፊነታቸዉ የተነሱት አመራሮች ለሶስት ዓመት የድርጅቱ ሰራተኞች ጭማሪ ሳይደረግ በፋይላቸዉ ላይ ጭማሪ እና ድጎማ አድርገናል ማለታቸውን ፣ የሰራተኛው ቅጥሩ ከ 1 ሺህ እስከ 2 ሺህ ብር ቢሆንም ዉሉ ላይ 6500 ብር ደመወዝ እንደሚከፍሉ ሲገልፁ እንደነበር ተነግሯል።
ላለፉት አራት ወራት ምርቱ ተቋርጦ የቆየዉ ሞሐ የለስላሳ መጦች ፔፕሲ፣ ኮካ ኮላ፣ ሚሪንዳ ኦሬንጅ፣ 7-አፕ፣ ሚሪንዳ ቶኒክ፣ ሚሪንዳ አፕል (ሁሉም የፔፕሲ ብራንዶች) እና ኩል የዉሃ ምርቶቹ ይታወቃል ።
ሞሐ በሀገሪቱ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ 52 በመቶውን የገበያ ድርሻ ይዞ የሚገኝ ግዙፉ አምራች ድርጅት ሲሆን በአዲስ አበባ ጎተራ ፣ ሰሚትና ተክለሃይማኖት በክልል ከተሞች በሐዋሳ ፣ መቐለ፣ ቡሬ እና ጎንደር እያመረተ ይገኛል።
