የቀድሞዋ የላይቤሪያ አቃቤ ሕግና ፍትሕ ሚኒስቴር ግሎሪያ ማያ ሙሱ-ስኮት

10 ጥር 2024, 18:30 EAT

የቀድሞዋ የላይቤሪያ አቃቤ ሕግና ፍትሕ ሚኒስቴር ግሎሪያ ማያ ሙሱ-ስኮት በዘመዳቸው ግድያ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈረደባቸው።

የላይቤሪያ ጉምቱ ዳኛ እና ፖለቲከኛ የነበሩት ሚኒስትሯ ለሴቶች መብት በመታገል ይታወቃሉ።

አሁን እሥር ቤት የሚገኙት የ70 ዓመቷ ሙሱ-ስኮት ፍርዱን ለመቀልበስ ይግባኝ እንደሚሉ ታውቋል።

የችሎቱ ዳኛ አሁን ጡረታ የወጡትን ሚኒስትር በ29 ዓመቷ ካርሎ ሙሱ ግድያ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ሰጥተዋል።

ችሎቱ እንደተመለከተው ሙሱ-ስኮት እና ሌሎች ሶስት ሴቶች ባለፈው ሰኔ “ፈቅደውና አውቀው በሟች ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት አድርሰዋል።”

ሟች ደረቷ አካባቢ የቆሰለች ሲሆን ግራና ቀኝ እግሮቿና ብብቷ አካባቢ በስለት ተወግታለች ይላል የክሱ መዝገብ።

የቀድሞዋ ሚኒስትር ግን መኖሪያ ቤታቸው የገባ “ገዳይ” እንጂ እሳቸው የገዛ ዘመዳቸውን እንዳልገደሉ ይናገራሉ።

በርካታ ላይቤሪያዊያን የቀድሞዋ የፍትሕ ሚኒስትር በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ በሰሙ ጊዜ ደንግጠው ነበር።

ለዚህም ነው የፍርድ ሂደታቸው የሀገሪቱ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመው።

አልፎም የፍርድ ሂደታቸው ካለፈው ታኅሣሥ ወር የሀገሪቱ ምርጫ ጋር ተገጣጥሟል።

የተመራጩ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ቦዋካይ ፓርቲ አባል የነበሩት ሚኒስትሯ የምርጫ ኮሚሽኑ ፓርቲዎች የመራጮችን ዝርዝር መመልከት እንዲችሉ እንዲፈቅድ ተከራክረዋል።

እንደ ሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሚኒስትሯ እና ሌሎች ሶስት ተጠርጣሪዎች ሲፈርድባቸው ደጋፊዎቻቸው በለቅሶ ነው የተመለከቱት።

ጡረታ እስከወጡበት የአውሮፓውያኑ 2003 ድረስ የላይቤሪያ ፍትሕ ሚኒስትር እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ሆነው አገልግለዋል።

ከጡረታ በኋላ ወደ ፖለቲካ እንቀስቃሴ ገብተው የሜሪላንድ ግዛት ሕግ አውጭ ሆነው እስከ 2012 ሠርተዋል።

ከዚያ በኋላ ደገሞ የሀገራቸውን ዲሞክራሲ ለመገንባት እና መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሕገ-መንግሥት ገምጋሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ቆይተዋል።

ጠበቃዋ አውግስቲን ፋያህ፤ በሚቀጥሉት ቀናት ይግባኝ እንደሚጠይቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጆርጅ ዊያህን የረቱት ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ቦአካይ በአውሮፓውያኑ ጥር 22 ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ።