የአል ሸባብ ታጣቂዎች

10 ጥር 2024, 19:25 EAT

የአል ሸባብ ታጣቂዎች ሁለት ሶማሊያዊያን እና ሌሎች በርካታ የውጭ ዜጎችን የያዘ ሄሊኮፕተር በቁጥጥር ሥር አዋሉ።

ሄሊኮፕተሩ ባጋጠመው የቴክኒክ እክል ምክንያት የኢስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል ሸባብ ቀጣና በሆነ ሥፍራ ለማረፍ ተገዷል ሲሉ አንድ ወታደራዊ መኮንን ተናግረዋል።

ሄሊኮፕተሩ ማዕከላዊ ሶማሊያ ከምትገኘው ቤሌድወይኔ ከተማ ተነስቶ ብዙም ሳይቆይ እክል እንዳጋጠመው ሜጀር ጄኔራል ሀሰን አሊ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ጄኔራሉ አክለው ሄሊኮፕተሩ ሂደንሬ የተባለ ሥፍራ ማረፉን ገልጠዋል።

“ሁለት ሶማሊያዊያን እና በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ሄሊኮፕተሩ ውስጥ ነበሩ። የሕክምና ቁሳቁሶችንም ጭኖ ነበር። ሄሊኮፕተሩ ከጋልጉዱድ ግዛት ቁስለኛ ወታደሮችን ይዞ መመለስ ነበር ዕቅዱ” ብለዋል።

ስማቸውን መግለጥ ያልፈለጉ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኛ ሄሊኮፕተሩ የመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያ ሚሽን ንብረት መሆኑን ጠቅሰው ከተሳፋሪዎች መካከል አምስቱ የውጭ ዜጎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጋልሙዱግ ክልል ፀጥታ ሚኒስትር መሐመድ አብዲ ሄሊኮፕተሩ በአል ሸባብ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ምንጮች ለሮይተርስ እንደገለጡት ሄሊኮፕተሩ በጠቅላላው 9 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።

ሄሊኮፕተሩ ባጋጠመው የቴክኒክ እክል ምክንያት ለማረፍ እንደተገደደ ቢዘገብም ሌሎች ሄሊኮፕተሩ በስህተት በአል ሸባብ ቀጣና ማረፉን ዘግበዋል።

አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ኢስላማዊ ቡድን ሲሆን፣ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። ቡድኑ በሶማሊያ ውስጥ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ በርካታ የቦምብ እና የደፈጣ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በኬንያ ውስጥ ተደጋጋሚ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ ጥቃቱ እስከ ኡጋንዳ ድረስ የዘለቀ ነው።

አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም በተደጋጋሚ ሲዝት የቆየ ቢሆንም ከሙከራ ያለፈ ጥቃት አድርሶ አያውቅም።

ነገር ግን ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ሰኔ አካባቢ ታጣቂዎቹ ያልተጠበቀ ጥቃት ፈፅመው ነበር።

አልሻባብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አስርጎ ያስገባቸው ታጣቂዎቹ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በወሰደው እርምጃ ወደ 200 የሚጠጉ የቡድኑ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።

በአል ሸባብ ቁጥትር ሥር ውሏል ስለተባለው ሄሊኮፕተር የሶማሊያ መንግሥትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።