ካርኪቭ የሚገኝ ሆቴል

ከ 5 ሰአት በፊት

በዩክሬን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ካርኪቭ የሚገኝ አንድ ሆቴል ላይ በተሰነዘረ ሁለት የሩስያ ሚሳኤሎች ጥቃት 11 ሰዎች መቁሰላቸውን የካርኪቭ ገዥ አስታወቁ።

ከዩክሬን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት የተገኙት ፎቶግራፎች እንደሚያሳዩት በሆቴሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የእሳት አደጋ ሠራተኞችን በቦታው ተገኝተዋል።

ገዥው ኦሌህ ስኔሁቦቭ እንደተናገሩት ከተጎጂዎች መካከል የቱርክ ጋዜጠኞች ይገኙበታል። ሆቴሉ በሁለት ኤስ-300 ሚሳኤሎች ተመትቷል።

ሩሲያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዩክሬን ከተሞች ላይ የምታደርሰውን የአየር ጥቃትን አጠናክራ ቀጥላለች።

የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳሉት በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሚሳኤሎች በደረሱት ጥቃቶች በደርዘን የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ተገድለዋል።

ከሩሲያ ድንበር በ30 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ካርኪቭ፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በ2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ መውረር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በደረሰባት የአየር ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዳለች።

በቅርቡ በተሰነዘረ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው የ35 ዓመት ግለሰብ በጠና ሁኔታ እንደሚገኝ ገዥው በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

የከተማው ከንቲባ ኢጆር ቴሬክሆቭን ጠቅሶ የዩክሬኑ ዩኒየን የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሆነ በወቅቱ በሆቴሉ ውስጥ ከ30 ሲቪሎች በስተቀር ምንም አይነት ወታደራዊ ኃይል አልነበረም።

በሆቴሉ በአቅራቢያው ባሉ በርካታ ቤቶችና መኪኖችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

የዜለንስኪ የአየር መከላከያ ጥያቄ

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ረቡዕ ዕለት በሊትዌንያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ምዕራባውያን አጋሮች ተጨማሪ የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን እንዲያቀርቡላቸው አሳስበዋል።

ኪዬቭ የሩስያን ጦር እንድትቋቋም ከዩክሬን ጎን ከቆሙ ጠንካራ አጋሮች አንዷ ሊትዌንያ ናት።

“ብዙ የአየር መከላከያ መሣሪያዎች የሉንም። ከድሮኖች ጋር የሚደረገው ትግልም ተመሳሳይ ነው። ከሊትዌንያ እና ከብዙ አጋሮች ጋር ስምምነት በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።

ሊቱዌንያ ጨምሮ ሁለቱ የባልቲክ ጎረቤቶቿ ላትቪያ እና ኢስቶኒያ የቀድሞ የሶቪየት ህብረት አባል ቢሆኑም አሁን የኔቶ አባላት ናቸው።

ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አንፃር ሊትዌንያ ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ የምትሰጥ ቀዳሚ አገር ነች ሲል የጀርመኑ ኪየል ዎርልድ ኢኮኖሚ ዘግቧል። አሜሪካ ለዩክሬን ጦር የምታደርገው አስተዋጽኦ ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።

ቭላድሚር ፑቲን “ዩክሬንን እስካላጠፋ ድረስ አይተኛምም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በኢንተርፋክስ-ዩክሬን በኩል ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

“እሱ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረን ይፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ አጋሮቻችን ለዩክሬን በሚሰጠው ፈጣን ወታደራዊ እርዳታ እና የገንዘብ ድጋፍ ጥርጣሬ ስለሚገባቸው ይህ ለሩሲያ ፌዴሬሽን ድፍረት እና ጥንካሬ ይሰጣል።”

“ሁላችንም አንድ ላይ እስክንጨርሰው ድረስ [የሩሲያው መሪ] ይህን [ጦርነት] አይጨርሰውም።” የባልቲክ ግዛቶች እና ሞልዶቫ “ቀጣይ ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉም” አስጠንቅቀዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የዩክሬኑ መሪ ወሳኝ የጦር መሳሪያ አቅርቦትን ለማስቀጠል ያለመ ጥብቅ ውይይት ከምዕራባውያን አጋሮች ጋር አድርገዋል። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ ኪዬቭ የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት ይህ ነው የሚባል መሻሻል ባለማሳየቱ አንዳንድ ምዕራባውያን የኪዬቭን ስትራቴጂ ከመጠራጠር ባለፈ የጦርነቱ ወጪም ስጋትን ፈጥሯል።

ሩሲያ በበኩሏ ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ለማድረግ ቁርጠኛ በመሆኗ የኔቶ አገሮች ተተኳሾችን እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ለማምረት እየታገሉ ነው።

ለዩክሬን እንዲሰጥ የጠየቀው 43 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የአውሮፓ ህብረት ጥቅል እርዳታ በሃንጋሪ ድምፍን በድምጽ መሻር መብት ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ልዩነቱ በሰፋው የአሜሪካ ኮንግረስ ምክንያትም ከዋሽንግተን የሚገኝ አዲስ ወታደራዊ ዕርዳታ ቆሟል ።