
ከ 5 ሰአት በፊት
በረዥም የሰላም ዘመን የምትታወቀውና ጦርነት ጨርሶውኑ እየረሳች መጥታለች የምትባለው ሰሜን አውሮፓዊቷ ስዊድን ከሰሞኑ ስለ ጦርነት በስፋት መነገሩ ዜጎቿን አስጨንቋል።
በተለይ የአገሪቱ ሁለት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ‘ስዊድን ለአይቀሬው ጦርነት መዘጋጀት አለባት’ የሚል ማስጠንቀቂያ ከተናገሩ በኋላ ጉዳዩ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል።
አንዳንዶች መጪው ዘመን ከ200 ዓመታት በላይ በሰላም ለኖረችው ስዊድን አስጊ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
የሲቪል መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ካርል ኦስካር ቦህሊን በአንድ የደኅንነት ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ‘ስዊድን በመጪው ዘመን ጦርነት ሊያጋጥማት ይችላል።’
ይህን ሐሳብ የሚጋሩት የጦሩ ዋና አዛዥ ጄኔራል ማይክል ባይደን ሁሉም ስዊድናዊያን ለጦርነት ቢያንስ የሥነ ልቡና ዝግጅት ያድርጉ ሲሉ አሳስበዋል።
ይህን የሁለቱን ወታደራዊ መኮንኖች ሐሳብ ‘ተጨባጭነት የሌለው’ ሲሉ ያወገዙት ተቃዋሚዎች በሰላም አገር የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ትክክል አይደለም ብለዋል።
የቀድሞዋ የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ማክደሊና አንደርሰን ለስዊዲን ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በአካባቢው የደኅንነት ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑ የማይካድ ቢሆንም ጦርነት ደጃችን መጥቷል ብሎ ማሰብ ግን ትንሽ የተጋነነ ነው።
ብሪስ (Bris) በሚል ምሕጻር የሚታወቀው በስዊድን የልጆች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልጆችና አዳጊዎች በቀጥታ ስልክ እየደወሉ መጪው ጦርነት እንዳሳሰባቸው ይነግሩናል ብሏል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ጥሪዎች ደርሰውት እንደማያውቁና ምናልባት ወጣቶች በቲክቶክና ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለ ጦርነት የሚያዩት ነገር እያስጨነቃቸው እንደመጣ እንገምታለን ብሏል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ማጃ ዳህል ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንዲህ ዓይነት የጦርነት ወሬ ለአዋቂዎች ይዘው ሲመጡ ለልጆች በምን መንገድ መነገር እንዳለበት ቀድመው ማሰብ ነበረባቸው ብለዋል።
- በሶማሊላንድ እና ሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እና ዛቻ እየተፈጸመብን ነው አሉ10 ጥር 2024
- “ከብሔራዊ ቡድኑ ራሴን ያገለልኩት ለሌሎች ዕድል ለመስጠት ነው”፡ ሽመልስ በቀለከ 5 ሰአት በፊት
- ከዋክብትን ከመግዛት የክለብ አውቶብሶችን ወደ መሸጥ የወረደው የቻይናው ሱፕር ሊግከ 6 ሰአት በፊት
ምንም እንኳ ይህ የጦርነት ስጋት ድንገት መነጋገሪያ ቢሆንም ጦርነትን ለረሱት ስዊድናዊያን የጦር መኮንኖቹ ማሳሰቢያ የማንቂያ ደውል ሆኗል።
ከሁለት ምዕተ ዓመት በላይ ደንበኛ ጦርነት ውስጥ ገብተው የማያውቁት ስዊድናዊያን ኔቶን ሙሉ በሙሉ ጫፍ ደርሰዋል።
የሚጠብቁት የቱርክ ፓርላማና የሐንጋሪ ፓርላማ ጥያቄያቸውን እስኪያጸድቅ ብቻ ነው።
የስዊድን የጦር አዛዥ ንግግራቸው አዲስ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ከወር በፊት ምሥራቅ ዩክሬንን የጎበኙት የጦር አዛዡ አገራቸው የዩክሬን ፓይለቶችን እንደምታሰለጥን ተናግረዋል። ስቶክሆልም ግሪፐን የተባሉ ተዋጊ ጄቶችን ለዩክሬን ለመስጠት እያሰበች እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ጄኔራል ባይደን እንደተናገሩት ስለ መጪው ጦርነት ስናገር ስጋት ለመጫር ሳይሆን ሁሉም ስዊድናዊ የራሱን የሥነ ልቡና ዝግጅት እንዲያደርግ ለማስቻል ነው ብለዋል።
ፊንላንድ ኔቶን በይፋ የመቀላቀሉን ሂደት ያጠናቀቀች ሲሆን ሞስኮ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ከወጡ ፊንላንድ ዋጋ ለመክፈል የመጀመርያዋ አገር ትሆናለች ስትል አስጠንቅቃለች።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ስዊድንና ሌሎች አጋር አገሮች በርካታ የጦር መሣሪያ እንዲያመርቱና በጋራ ጠንካራ ኃይል እንዲገነባ እንደሚሹ አስገንዝበዋል።
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስተርሰን በበኩላቸው በያዝነው የፈረንጆች ዓመት አገራቸው ኔቶ ያስቀመጠውን የወታደራዊ ወጪ መጠን እንደሚያሟሉ ቃል ገብተዋል።
ኔቶ አገሮች ከጠቅላላ ዓመታዊ ጥቅል ምርታቸው 2 እጁን ለወታደራዊ ወጪ እንዲያውሉ ይፈልጋል። ስዊድን በዚህ ስሌት ለወታደራዊ ወጪ ከዚህ ቀደም ከምትመድበው እጥፍ ገንዘብ መመደብ ትጀምራለች ማለት ነው።
ኦስካር ጆንሰን የተባሉ በስዊድን መከላከያ ዩኒቨርስቲ የጦር ጉዳዮች ተንታኝ እንደሚሉት አሁን በስዊድን የሚወራው የጦርነት ስጋት ‘አይሆንም የሚባል አይደለም’ ይላሉ። ይሁንና ስጋቱ ሊያጋጥም የሚችለው ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ጦርነት ሲቋጭና ሠራዊቷን በድጋሚ ስትገነባ እንዲሁም አሜሪካ የተባበሩት አውሮፓ አገራትን በጦርነት መርዳት ስታቆም ሊሆን የሚችል ስጋት ነው።
“እነዚህ ነገሮች አይሆኑም አይባልም፤ ሊከሰቱ ይችላሉ” ይላሉ ኦስካር ጆንሰን።
ስዊድን ለመጨረሻ ጊዜ ጦርነት የገጠማት ከጎረቤት ኖርዌይ ጋር ለአጭር ጊዜ ሲሆን ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ በ1814 ዓ/ም ነበር።
ስዊድን በ2ኛው የዓለም ጦርነት ገለልተኛ አገር ነበረች።