January 11, 2024 – Konjit Sitotaw 

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷ ተገለፀ።

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 አመት 1.59 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በማጣት ከሩሲያ በመቀጠል ከአለም ከፍተኛ ገንዘብ ያጣች ሀገር መሆኗ ተገልጿል።

በዓለም ዙሪያ የኢንተርኔት ደህንነትና ነጻነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን እና ምርምሮችን በመስራት የሚታወቀው ቶፕ ቴን ቪፒኤን የተባለው ተቋም በሰራው ጥናት መሰረት በፈረንጆቹ 2023 በኢትዮጵያ ለ3,414 ሰዓታት የኢንተርኔት አገልግሎት ሲቋረጥ ፥ ለ11,496 ሰዓታት የማህበራዊ ሚዲያ መዘጋትቱንም አሳውቋል።

በተቋሙ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት 1.59 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷ ሲጠቆም ይህም በአለም 4 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች ከተባለችው ሩሲያ በመቀጠል ከፍተኛ ገንዘብ ያጣች ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች።

በኢትዮጵያ የፌስቡክ፣ የዩቲዩብ፣ የቴሌግራም እና የቲክቶክ አገልግሎት በሀገሪቱ በተፈጠረ ሃይማኖታዊ ውዝግብ ምክንያት የተነሳ አገልግሎቱ መገደቡን ያስታወቀው ተቋሙ እገዳው 5 ወር ለሚጠጋ ጊዜ በመቆየቱ ምክንያት የቪፒኤን ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በዓመቱ መጨመሩን አስታውሷል።

ተቋሙ በኢትዮጵያ በነሀሴ ወር 2015 ዓ/ም መጀመሪያ ላይ በሰሜናዊው የአማራ ክልል አካባቢ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንም ሲጠቅስ ሀገሪቱ በ2023 በአጠቃላይ 29.8 ሚሊዮን ህዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ የገጠማቸው መሆኑን ጠቅሷል።

ተቋሙ በ2023 በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት በአጠቃላይ 9.01 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ አጥተዋል ያለ ሲሆን በ25 አገሮች ውስጥ 196 ዋና ዋና የኢንተርኔት መቆራረጦች መመዝገቡንም አሳውቋል።