
11 ጥር 2024, 13:21 EAT
ሶማሊያዊያን ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችውን ስምምነት በመቃወም “ዋን ሚሊዮን ማርች” የተሰኘ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ናቸው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ሞጋዲሾ ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊንዱ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የገቡትን ስምምነት ተቃውመዋል።
በስምምነቱ መሠረት ሶማሊላንድ የኤደን ባሕረሰላጤ ላይ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የምትሰጣት ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ለሶማሊላንድ እውቅና ትሰጣለች።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ለሶማሊላንድ እውቅና ይሰጣል ወይ የሚለው ገና ምላሽ አላገኘም።
ብሔራዊው የሶማሊያ ጣቢያ ሶማሊ ብሔራዊ ቲቪ ተቃዋሚዎች ተሰባስበው ሀገራዊ ሙዚቃ እያሰሙ ሰልፉን ሲታደሙ አስመልክቷል።
በርካታ መንገዶች ለዚህ ሰልፍ ሲባል እንደተዘጉና የፀጥታ ሁኔታው እንደተጠናከረ ቢቢሲ ሶማሊ ተመለክቷል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሕመድ ሞዐሊም ፊቂ በሞጋዲሾ ጎዳና ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ማሰማታቸውን ሶማሊ ብሔራዊ ቲቪ ዘግቧል።
“በሕይወት እስካለን ድረስ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መሬት ምንም አትነካም” ሲል አንድ ሰልፈኛ መናገሩን ጣቢያው አሳይቷል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ሶማሊያን የሚያሞግሱ ዘፈኖች በመዝፈን ‘የሶማሊያ ሕዝብ አገሩን ይከላከላል’ ሲሉ መፈክር አሰምተዋል።
የመረጃ ሚኒስትር ዳውድ አዊስ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት “የኢትዮጵያን ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ለመቃወም ነው።”
የሶማሊያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውም ገልጸዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ፣ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ማሕሙድ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ መንገድ እንዲከተሉና ወደተካረረ ሁኔታ ከሚያመራ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የሶማሊያን የግዛት አንድነት እንደሚያከብርም አክለዋል።
- ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ እውቅና ማግኘትን ለምን አጥብቃ ፈለገች?6 ጥር 2024
- የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር እና ተሳፋሪዎች በአል ሸባብ ቁጥጥር ሥር ዋሉ11 ጥር 2024
- በሶማሊላንድ እና ሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እና ዛቻ እየተፈጸመብን ነው አሉ10 ጥር 2024
ስምምነቱ ምን ይላል?
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በገቡት የመግባቢያ ሰነድ ቃል በቃል ምን እንደሚል ለሕዝብ ይፋ ስላለሆነ ግልፅ አይደለም።
ለዚህም ነው ከኢትዮጵያና ከሶማሊላንድ መንግሥታት የተለያዩ መግለጫዎች ሲወጡ የሚስተዋሉት።
የመግባቢያ ሰነድ የግዴታ ተፈፃሚነት ያለው ሰነድ አይደለም። ነገር ግን ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለማከራየት ዝግጁ እንደሆነች አሳይታለች።
ስምምነቱ ወታደራዊ ትብብርንም ያቀፈ ነው። ሶማሊላንድ የባሕር በሯን ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ልታከራይ እንደሆነ ተናግራለች። ይህን አዲስ አበባም አረጋግጣለች።
በምላሹ ሶማሊላንድ ከአትራፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አክሲዮን ልታገኝ እንደምትችል ተሰምቷል።
ነገር ግን ነገሮች የተወሳሰቡት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች ወይ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው። የቀድሞዋ የብሪታኒያ ግኝ ግዛት የነበረችው ሶማሊላንድ ራስ ገዝ ከሆነች 30 ዓመት ቢያልፋትም ዕውቅና ማንም ሰጥቷት አያውቅም።
ስምምነቱ በተፈረመ ወቅት የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ ለሀገራቸው ወደፊት ዕውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ ይህን ጉዳይ እስካሁን አላረጋገጠችም። ባይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከስምምነቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ “ለሶማሊላንድን ዕውቅና መስጠትን በተመለከተ አቋም ለመያዝ” መስማማቱን ገልጧል።
አከራካሪ የሆነው ለምንድን ነው?
ሶማሊላንድ ማለት ለሶማሊያ የግዛት አንድነቷ አንድ ትልቅ አካል ናት። ሶማሊላንድ ከየትኛው ሀገር ጋር የምትገባው ስምምነት ያለሞጋዲሹ ይሁንታ መሆኑ ለሶማሊያ አደጋ ነው።
የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመ ማግስት ሶማሊያ ስምምቱን “የወረራ ድርጊት” ነው በማለት “ሰላምና መረጋጋትን” ሊያናጋ እንደሚችል ጠቅሳ ነበር።
በስምምነቱ እጅግ የተቆጣችው ሶማሊያ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ እስከ መጥራት ደርሳለች።
ባለፈው ሰንበት የሶማሊያው ፕሬዘደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ “ሀገራችንን በምንችለው መንገድ እንመክታለን። የትኛውም ሊረዳን የሚችል አካል ካለ ለመተባበር ዝግጁ ነን” ብለዋል።
ወጣቶች “ሀገራችንን ለመጠበቅ ዝግጁ ሁኑ” የሚል መልዕክትም አሰምተዋል።
ባለፈው ሳምንት በሞጋዲሹ ስምምነቱን የሚቃወም ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጥተዋል።
ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ነፃ መውጣቷን ያወጀችው በአውሮፓውያኑ 1991 ነው። ሀገር መሆን የሚያስችላት ቁመና አላት። ማለትም የፖለቲካ ሥርዓት፣ መደበኛ ምርጫ፣ የፖሊስ ኃይል እና የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።
ባለፉት አሥርት ዓመታት ሶማሊያ በግጭት ስትናወጥ ሶማሊላንድ በተነፃፃሪው ሰላማዊ ጊዜ አሳልፋለች።
ነገር ግን የሶማሊላንድ ሀገር መሆን በየትኛውም ውጫዊ ወገን ዕውቅና አግኝቶ አያውቅም።
ሶማሊላንድ እንዳለችው ኢትዮጵያ ዕውቅና ብትሰጣት ይህ ውሳኔ በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖረዋል።