
10 ጥር 2024
የዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ባሕር ኃይል አባላት ሁቲ ታጣቂዎች ቀይ ባሕር ላይ ሊያደርሱ ያሰቡትን ከፍተኛ ጥቃት ማክሸፋቸውን ዩኬ ገለጠች።
የዩኤስ መከላከያ ሠራዊት እንደገለጠው በኢራን የሚደገፉት የሁቱ አማፂያን ለሊቱን 21 ጊዜ የድሮንና የሚሳዔል ጥቃት ሰንዘረዋል።
ጄቶች እና አራት የጦር መርከቦች ጥቃቱን ማክሸፋቸውን የገለጠው የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በጥቃቱ ማንም የተጎዳ የለም ብሏል።
የሁቲ አማፂያን ስለጥቃቱ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም። ነገር ግን በጋዛ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በቅርቡ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ከርመዋል።
አማፂያኑ ጥቃት የተሰነዘረባቸው መርከቦች የእስራኤል ንብረቶች ናቸው ቢሉም አንዳንዶቹ መርከቦች ንብረትነታቸው የሌላ ሀገር ሆኖ ተገኝቷል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጠው ማክሰኞ የተሰነዘረው ጥቃት ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 19 በኋላ ለ26ኛ ጊዜ የተደረገ ነው።
ዕዙ እንዳስታወቀው በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር ማክሰኞ ምሽት 3፡15 ገደማ ኢራን ሠራሽ ድሮኖች፤ ፀረ-ክሩዝ ሚሳዔል እና ፀረ-መርከብ ባለስቲክ ሚሳዔሎች ተተኩሰዋል።
ሚሳዔሎቹ የተተኮሱት በሁቲ አማፂያን ቁጥጥር ሥር ካለው የየመን ድንበር ሲሆን አቅጣጫውን ወደ ዓለም አቀፍ መርከቦች መመላለሻ ያደረገ ነው።
- በሶማሊላንድ እና ሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እና ዛቻ እየተፈጸመብን ነው አሉ10 ጥር 2024
- የኤኳዋዶሩ ፕሬዘደንት በታጠቁ ነውጠኛ የዕፅ አዛዋዋሪ ቡድኖች ላይ ጦርነት አወጁ10 ጥር 2024
- አንዱ የሰውነት አካል ከሌላው አንጻር በፍጥነት እያረጀ መሆኑን ማወቅ ይቻላል?10 ጥር 2024
18 ድሮኖች፣ ሁለት ክሩዝ ሚሳዔሎች እና አንድ ባለስቲክ ሚሳዔል በኤፍ/ኤ 18 የጦር አውሮፕላኖች ተመትቶ እንደወደቀ ተዘግቧል።
ኤችኤምኤስ የተሰኘችው የጦር መርከብ ሰባት የሁቲ ድሮኖችን መትታ መጣሏን አንድ የብሪታኒያ መከላከያ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የሁቲ አማፂያን ጥቃቱን የሚቀጥሉበት ከሆነ ትሩፋቱን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው” ሲሉ የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ በመግለጫቸው አስጠንቅቀዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ዩኤስ እና ጨምሮ እንዲሁም ጀርመን፣ ጣሊያን፣ አውስትራሊያ፣ ባሕሬን እና ጃፓንን ጨምሮ 10 አጋር ሀገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ የሁቲ አማፂያንን አስጠንቅቀዋል።
ሀገራቱ በመግለጫቸው የመን የሚገኘውን የሁቲ አማፂያን የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ሊመቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
የሁቲ አማፂያን ጥቃት “የዓለም አቀፍ ንግድ ቁልፍ የሆነውን የባሕር እንቅስቃሴ እየገታ ነው” ብለዋል።
የዓለም 15 በመቶው የባሕር ላይ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄደው ቀይ ባሕር ላይ ሲሆን ይህ መስመር ከሜዲቴራኒያን እና ሱዌዝ ካናል ጋር ይገናኛል።
ይህ ቀጣን በአውሮፓ እና እስያ መካከል ያለውን ንግድ የሚያቀላጥፍ ነው።
በቀድሞው ስማቸው አንሳር አላህ ተብለው የሚጠሩት የሁቲ አማፂያን የየመን ዛይዲ ሺያ አናሳ ሙስሊሞችን ይወክላሉ።
አማፂያኑ ባለፈው ጥቅምት በጋዛ የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ የእስራኤል ንብረት የሆኑ መርከቦችን ብቻ እንደሚያጠቁ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ የኢራን መንግሥት ድሮኖችን ጨምሮ ክሩዝ እና ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ለሁቲ አማፂያን በድብቅ ያቀርባል ሲሉ ይወቅሳሉ። ይህ የተባበሩት መንግሥታት ሕግን የሚጣረር ነውም ይላሉ።
የኢራን መንግሥት ይህን ወቀሳ አይቀበለውም።