January 11, 2024 

ያለፉት 3 ዓመታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በእጅጉ የተፈተነበት ነው- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ “ያለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በእጅጉ የተፈተነበት እና ያለፈበት ነው” አሉ።

ፕሬዝዳንቷ በዛሬው እለት በተከፈተው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት አውደርዕይ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲን በተመለከተ ለህዝብ ግልፅ መረጃዎች መስጠት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።

እንደኢትዮጵያ ያለ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ስርዓት በሌላቸው ሀገራት ጭምር የዲፕሎማሲ ስራዎች ለህዝብ በተደጋጋሚ ይፋ ይደረጋሉ ያሉት ፕሬዝዳንቷ ኢትዮጵያም ለዚህ ትኩረት መስጠት አለባት ብለዋል።

ውስብስብ እና ተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አካሄድ መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ የ21ኛው ክፍለ ዘመንን ወደሚመጥን የዲፕሎማሲ ሂደት ለማሸጋገር ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የ116 ዓመታት የዲፕሎማሲ ስራን የሚያሳይ አውደርዕይ “ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን” በሚል ርዕስ ሃሳብ ተከፍቷል።

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ አምባሳደሮች ፣ ዲፕሎማቶች፣ የዓለምአቀፉ ተቋማት ተጠሪዎች ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሪዎች እንዲሁም የዘርፉ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ተገኝተውበታል።