
ከ 3 ሰአት በፊት
በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ደምቢ ዶሎ ከተማ በመማርያ ክፍል ውስጥ የክፍል ጓደኛቸውን በቡድን የደፈሩት ሁለት ተማሪዎች በእስራት ተቀጡ።
በደምቢ ዶሎ ከተማ የፋሲሎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑት ሰቦና ዲሪብሳ እና ኤቢሳ አድማሱ የክፍል ጓደኛቸውን በቡድን በመድፈራቸው አምስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የፍርድ ሂደቱን የመሩት ዳኛ ምትኩ ወዳጆ “ተበዳይዋ ተማሪ ስትሆን የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙትም የክፍል ጓደኞቿ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ወንጀል የተፈጸመው ተበዳይዋ የውጤት ስህተት ለማስተካከል ሰኔ 9/2015 ዓ. ም. ትምህርት ቤት በሄደችበት ወቅት ነው።
“ውጤት ለማስተካከል ትምህርት ቤት በሄደችበት ወቅት ብዙ ተማሪ አለመኖሩን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው እያጫወቱ ወደ ክፍል ውስጥ ካስገቧት በኋላ በር ዘግተው የመድፈር ወንጀል ፈጽመውባታል” ብለዋል ዳኛ ምትኩ ወዳጆ።
ሁለተኛ ተከሳሽ የክፍሉን በር ሲዘጋ የመጀመሪያ ተከሳሽ የመድፈር ወንጀል ፈጽሟል። ከአንደኛ ተከሳሽ በመቀጠልም ሁለተኛው ተከሳሽ በድጋሚ የወንጀል ድርጊቱን በ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ላይ መፈጽሙን የሰዮ ወረዳ ፍርድ ቤት መዝገብ ያሳያል።
- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የግብጹን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተቀብለው አነጋገሩከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በየመን በሁቲ አማጽያን ላይ የአየር ጥቃት ከፈቱከ 4 ሰአት በፊት
- ብሩንዲ ‘መጥፎ ጎረቤት’ ካለቻት ሩዋንዳ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋችከ 5 ሰአት በፊት
“ወንጀሉ ሲፈጸም ልጅቷ የድረሱልኝ ጩኸት ስታሰማ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ ከባድ ዝናብ እየዘነበ ስለነበረ ድምጿን ማንም አልሰማም” በማለት ዳኛው ጨምረው ተናግረዋል።
ተበዳይዋ የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመባት በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቷ ሄዳ መቆየቷን ዳኛው ይናገራሉ። “ከዛ በኋላ ግን ሕመም ሲሰማት የደረሰባትን ለርዕሰ መምህሩ ተናገረች” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚያም የደምቢዶሎ ከተማ ፖሊስ ምርመራ አካሂዶ ዐቃቤ ሕግ በሰዮ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ መመሥረቱን ዳኛ ምትኩ ይናገራሉ።
ሁለቱ ተማሪዎች የተከሰሱበት አንቀጽ በ1996 በወጣው አገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 620/1 መሠረት ከአምስት እስከ 15 ዓመት እንደሚያስቀጣ ገልጸዋል። ተከሳሾች የወንጀል ማቅለያ ከግምት ገብቶላቸው ፍርድ ቤቱ ታኅሣሥ 25/2016 ዓ. ም. በዋለው ችሎት ሁለቱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በአምስት ዓመት ከስድስት ወር በእስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ተናግረዋል።
“እነዚህ ወጣቶች ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈጽመው ስለማያውቁ እንደ ቅጣት ማቅለያ ተወሰዶላቸዋል። በዐቃቤ ሕግ በኩልም ቅጣት ማጠናከሪያ ተብሎ የቀረበ አስተያየት ስለሌለ ሌሎችን ያስተምራል የተባለ ቅጣት” መተላለፉን ዳኛው ተናግረዋል።