January 12, 2024 – Konjit Sitotaw
. “የሰላም ሚኒስቴር ‘አስፈላጊነት አይታየንም’ የሚሉ ኃይሎች ተበራክተዋል” – የፓርላማ አባል
. “ተቋሙ ‘አሁን ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም?’ የሚለውን ፓርላማው ራሱ ቢያየው ነው ትክክል የሚሆነው” – የሰላም ሚኒስትር
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ሐሙስ ጥር 2፤ 2016 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እና ማብራሪያ አዳምጧል። በዚሁ ስብሰባ ላይ ጥያቄያቸውን ካቀረቡ የፓርላማ አባላት ውስጥ ሁለቱ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰላምን የማረጋገጥ ተልዕኮውን በአግባቡ አልተወጣም ሲሉ ተችተዋል።
ሉባባ ሰኢድ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል “የሰላም ሚኒስቴር ሲባል ከመቼውም [ጊዜ] በላይ ያላሰለሰ የህዝብ ውይይት በማድረግ ችግሩን በመቀነስ፣ ህዝባችን የናፈቀውን እንከን የለሽ ሰላም ያረጋግጣል የሚል ትልቅ እምነት ቢጣልበትም፤ እንዳለመታደል ሆኖ ችግሮች እየተባባሱ መጥተው ወደ ጦርነት እያመሩ ህዝባችንን የበለጠ የጨለመ ተስፋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል” ብለዋል።
ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡት አቶ አበባው ደሳለውም፤ “የሰላም ሚኒስቴር ያለውን አስተዋጽኦ ስናይ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ርዕዩን እና ተልዕኮውን አልተወጣም። ስልጣን እና ተግባሩን አንዳቸውንም በአግባቡ አልፈጸመም” ሲሉ የነቀፉት የፓርላማ አባሉ፤ “ለዚህ ተቋም የሚውለው ሃብት ለሌሎች የልማት፣ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት መዋል አለበት” ብለዋል።
