January 12, 2024

በአዲስ አበባ ታሪካዊ ቅርሶች መፍረስ እና በሂደቱ ለንፁሀን ሞት ምክንያት የሆኑ አካላት በህግ ይጠየቁ- ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ

ጥንታዊው ሎምባርዲያ የተሰኘ ህንፃ ከሰሞኑን መፍረሱን ተከትሎ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሦስት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው አንድ ሰው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ህይወቱ ማለፉን ዛሬ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ይህን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ ቅርሶች መፍረስ እና በዚህ ሂደት ውስጥም ለጠፋው የሰው ህይወት ምክንያት የሆኑ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ሲል አሳስቧል።

በዋና ከተማዋ ውስጥ እየወደሙ ያሉ ቅርሶችን በተመለከተ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ ይገባል ያለው ባልደራስ ፓርቲ፤ “ኦነግ/ ኦህዴድ/ ብልፅግና ስብስብ” በማለት የጠራውን ቡድን ለታሪካዊ ቅርሶች መፍረስ ወቅሷል።

ፓርቲው እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ ከፈረሱ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ፒያሳ የሚገኘው የእየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ህንፃ፣ የአዲስ አበባ ቴሌ መስሪያ ቤት ህንፃ እና የቻርለስ ደጎል መታሰቢያ ሐውልትን ጠቅሷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) በተመለከተ ከዚህ ቀደም ለማፍረስ የተደረገው ሙከራ እንዲቀር ተደርጓል ያለው ባልደራስ ሙሉ በሙሉ ውሳኔው ስለመቅረቱ ወደፊት የሚጣራ ነው ብሏል።