EOTC TV

መደፋፈሩ በዝቷል። መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱን ደፍሯታል። አልፎ ይሔዳል። ቤተ ክርስቲያንን መድፈር አደጋ ነው። አቡነ አብርሃም ( የተናገሯቸው ዝርዝር ነጥቦች)

January 12, 2024 

ዛሬ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

ብፁዕነታቸው በመግለጫቸው ፤ ” በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያኗ የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመዋታል ፤ በየግል በተለያዩ አባቶች፣ በተለያዩ መንገዶች በሚሰበኩ ስብከቶች ፣ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ፣ ለምን ? እንዴት ? ዝም አልሽ ቤተክርስቲያን በሚልም ትልቅ ፈተና ላይ ነች ” ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ፈተናዋን እንዴት ማለፍ እንዳለባት በጸሎት እግዚአብሔርን እንጠይቀዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

” ባለፈው የተለያዩ አባቶች በተለያየ መንገድ ተናገሯቸው ስለተባሉት ጉዳዮች ተነስቶ መንግስት ቀየሜታውን ገልጾ ቤተክርስቲያን መልስ እንድትሠጥበት አሳስቧል ” ያሉት ብፁዕነታቸው ” ቤተክርስቲያንም በስፋት፣ በትኩረት ተወያይታበታለች (ቅዱስ ቋሚ ሲኖዶስ) ይሁን እንጂ የብፁዓን ሊቃነጳጳሳት ጉዳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይ ነው የሚሆነው ፣ ምክንያቱም አንድ ሊቀ ጳጳስ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስለሆነ፤ ቀርቦ ተጠይቆ አውንታዊ መልስ ሰጥቶ ስህተት ነው ? እውነት ነው ? ብሎ የሚወሰን እንጂ ብግድ ተብሎ በቋሚ ሲኖዶስ ወይም በሌላ የተለያየ መልኩ እንዲህ ነው እንዲያነው ብሎ መናገር ህገ ቤተክርስቲያናችን አፈቅድም ” ብለዋል።

” ቤተክርስቲያን ሰላምን መፈለግ ፣ መሻት ፣ መልካም ነገር ማድረግ ነው ከዚህ ውጭ ሌላ አቋም የላትም ” ያሉት ብፁዕነታቸው ፤ ” እንደ ህግ እና ስርዓታችን በአባቶች ደረጃ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስነውን ይወስናል። ይህ ቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ ሲኖዶስ ተወያይቶ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚለውን እንዲል አልፎታል ” ሲሉ አሳውቀዋል።

ብፁዕነታቸው ፤ ” አሁን ግራ የሚያጋባው ትላንት ለበዓለ ጥምቀቱ የተሰየመው አብይ ኮሚቴ ከከተማ አስተዳደሩ፣  ከሚመለከታቸው የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ፣ከታላላቅ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ይህ ከባድ ፈተና እየተነሳ እንዳለና አሁንም በዓለ ጥምቀቱን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ቤተክርስቲያኒቱ እንዲህ አይነቱን ለይታ እንድታወግዝ ፣ የራሷን መልዕክት እንድታስተላልፍ በመንግሥት አቋም ተይዞ ለአብይ ኮሚቴው ተነግሯል ” ብለዋል።

” ቤተክርስቲያን ያራሷ ነፃነት አላት ፣ የራሷ ክብር አላት ፣ የራሷ ነፃ መድረክ ፈላጊ ናት ሁሉም እየተነሳ ያም ይሄን አድርጊ፣ ይሄም ይሄን አድርጊ ስላላት እየተጎተተች የተባለችውን አታስተናግድም ” ሲሉ ገልጸዋል።

” ክፉውን ክፉ፣ በጎውን በጎ፣ መልካሙን መልካም ፤ መልካም ያልሆነውን መልካም አይደለም ብላ ለማስተላለፍ የራሷ ህግ ስርዓት አላት ” ብለዋል።

” የፈለገ የሚያዛት ፣ የፈለገ የሚያሽከረክራት ፣ ያልወደደ እንደ ወደደ ፍላጎቱን ምኞቱን እንድትፈፅምለት የሚጎትታት ቤተክርስቲያንን ኖራም አታውቅም ወደፊትም ልትኖር አይገባም ” ሲሉ ተናግረዋል።

” ቤተክርስቲያን በራሷ ነፃ መድረክ ቆማ ችግሩን ችግር ነው ብላ መናገር አለባት እያደረገችም ነው። ” ያሉት ብፁዕነታቸው ” ይሄ በፍፅሙ አይመጥነኝም። እንዲህ አይነቱ የኔ ቃል አይደለም ብላ ታውጃለች ግን በግልፅ መጠየቅ ያለባትን ጠይቃ መናገር ያለበትን እንዲናገር ፈቅዳ ሁሉን ነገር በአግባቡ ታደርጋለች እንጂ በኩርፊያ በአላስፈላጊ ብሂል ይሄን ካላደረግሽ በዓል ለማክበር አልችልም ፣ ከናተ ጋር ግንኙነት የለንም እስከሚባል ድረስ የሚኖረው ነገር ከማንም ከምንም በፍፁም አይጠበቅም ” ሲሉ አሳውቀዋል።

“ከሃይማኖቴ ጋር የእኔ ነፍስ ትወጣለች። በሃይማኖት አንደራደርም” አቡነ አብርሃም

ትናንት ከቆሙበት የመስቀል ዐደባባይ ዛሬም ያልወረዱ አባት። ቤተ ክርስቲያን የሕልውና አደጋ ስለደረሰባት ለመጨረሻው ጸዋትወ መከራ እንዘጋጅ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመግለጫቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች

+ + + + +

፩. ቤተ ክርስቲያን የራሷ ነፃነት አላት

፪. ያም ይኽንን አድርጊ ይሄም ይኽንን አድርጊ ስላላት እየተጎች የተባለችውን የምታስተናግድ አትኾንም አይደለችምም።

፫. ማንም ይኽን አድርጊ እያለ ሊጎትታት አይችልም። ነገር ይኽንን በሉ ይኽንን ካላደረጋችሁ የሚባል መያዣ ነገር ቤተ ክርስቲያን አስተናግዳም አታውቅም። ወደፊትም አታስተናግድም። ወደፊትም የመጣውን በጸጋ ከምትቀበል ውጭ። ይኽንን አድርጊ ስልሽ ብቻ ነው የምታደርጊው የሚለው አስተሳሰብ ጨርሶ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ይነካል።

፬. መንግሥት በዓለ ጥምቀትን ለማክበር ቅድመ ኹኔታ ማስቀመጡን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። [የአቡነ ቄርሎስን እና የአቡነ ሉቃስን] አቋም በበዓሉ እንድታወግዝ መንግሥት አቋም ይዟል።

፭. መንግሥት አኩራፊ ሊኾን አይገባውም። ይኼንን ካላልሽ እንዲህ አላደርግም ማለት አይገባም።

፮. ሱሪ በአንገት አውጣው የሚባል ነገር ቤተ ክርስቲያን አትሸከምም

፯. መኪና ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ሲገባ የማይፈትሹ ሲወጣ የሚፈትሹ የመንግሥት ጥበቃዎች አሉ። የሚገባ መኪና አይፈተሽም የሚወጣ መኪና ይፈተሻል። ምንድን ነው የተፈለገው? ከቤተ ክርስቲያንስ ምንድን ነው የሚወጣው? መድፍ ነው? መሣሪያ ነው?

እኛ መሪዎቹ የማናውቀው ፈታሽ አቁሞ መፈተሽ ድፍረት ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕልውና መፈታተን ነው።

፰. መደፋፈሩ በዝቷል። መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱን ደፍሯታል። አልፎ ይሔዳል። ቤተ ክርስቲያንን መድፈር አደጋ ነው። ለሃይማኖቱ የማይሞት የለም።

አዛዣችን በዝቷል። ላዘዘን ኹሉ አጎንብሰን እንችላለን እንዴ? ሃይማኖታችን ከሚፈቅደው ውጭ። በሉ የተባልነውን ኹሉ ማለት እንችላለን እንዴ? ለእኔ አድርግ የሚለኝ ሃይማኖቴ ብቻ ነው። ማስፈራሪያ አይገዛንም። ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለው።

፱. በየሔድንበት በየቢሮው ደሞ ለኦርቶዶክስ? እየተባልን ነው። ቢያንስ አይኾንም እንኳ [የአባት ነው] አትቁም ያሉት ለማኝ አትቁም ነው። ያንን ያንን ያርሙ።

እዚህ እኛው ቤት አድር ብዬው ቅጥረኛው ስለሚበዛ ነው። የድፍረት ኃጢአት በዝቷል። ድፍረት የቤቱን ሰው ገዝቷል የውጭውንም ሰው ገዝቷል። የማትደፈረውንም ቤተ ክርስቲያን እያስደፈረ ይመጣል። አኹን የቀረው በሉ ውጡ ብሎ የመረካከብ ሥራ ነው ይኽች ቤተ ክርስቲያን የቀራት። ይኽንን ደግሞ ቆሞ የሚያይ የለም።

የጎጠኝነቱ ምንጩ ቤተ ክህነቱ ኾኗል። ከሃይማኖቴ ቋንቋዬ ይበልጣል የሚሉ ሰዎች የተነሡበት ጊዜ ነው። ስወለድ ቋንቋዬን ይዤ ነው የተወለድኹት ሃይማኖት በኋላ ነው የመጣ ነው የሚሉ ካህናት የተፈጠሩበት ወቅት ነው።

፲. ከሃይማኖቴ ጋር የእኔ ነፍስ ትወጣለች። በሃይማኖት አንደራደርም።

አንበርክኬ ልግዛ የሚለው ይቁም

ለመጨረሻው ጸዋትወ መከራ ራሳችንን እናዘጋጅ!

በተጨማሪም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን በተመለከተ የተናፈሰውን ወሬ በጸና ቃል እስከሞት በሚደርስ ትምምን በመግለጽ በትነውታል።