የወባ ትንኝ

12 ጥር 2024, 14:55 EAT

ከሰሀራ በታች የምትገኘው አፍሪካዊቷ ሀገር ኬፕ ቨርድ በ50 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ከወባ በሽታ ነፃ መውጣቷን አወጀች።

ኬፕ ቨርድ ባለፉት ሶስት ዓመታት ምንም ዓይነት የወባ በሽታ ያልታየባት ሀገር መሆኗን ያጤነው የዓለም ጤና ድርጅት ከወባ ነፃ የሚለውን ስም ሰጥቷታል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ይህ ትልቅ እመርታ ነው ይላሉ።

የወባ በሽታ በአፍሪካ ገዳይ ከሚባሉት አንዱ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2022 በአፍሪካ 580 ሺህ ሰዎች በወባ በሽታ ምክንያት ሞተዋል። ይህ ከተቀረው ዓለም ሲነፃፀር 95 በመቶውን ይይዛል።

በሽታው የሚነሳው ውስብስብ በሆነ ፓራሳይት ሲሆን የሚዛመተው ደግሞ በትንኝ ነው።

ምንም እንኳ በአንዳንድ ቦታዎች የወባ ክትባት እየተሰጠ ቢሆንም የበሽታው ዋነኛ መፍትሔ ትንኟን ማጥፋትና በሽታውን መቆጣጠር ነው።

ከአፍሪካ ድንበር በስተምዕራብ የምትገኘው ትንሿ ደሴት የጤና ሥርዓቷን በማጠናከር እና የጤና አገልግሎት ለሁሉም እንዲዳረስ በማድረግ ነው ለዚህ ስኬት የበቃችው።

የቁጥጥር መኮንኖች በሽታው ከመስፋፋቱ በፊት እየተቆጣጠሩ ትንኟን ለማጥፋት ሲጥሩ ነበር።

ኬፕ ቨርድ በሽታውን ለማጥፋት ቆርጣ በመነሳቷ ለዜጎቿ ብዛ ሳይሆን ከሌሎች ሀገራት ለሚመጡ ተጓዦችና ስደተኞችም ነፃ የሕክምና አገልግሎት ትሰጣለች።

ይህን የምታደርገው ከአህገረ አፍሪካ የወባ በሽታ መጥቶ እንዳይስፋፋ ለማገድ ነው።

“ይህ ስኬት የጤና ባለሙያዎች፣ ተባባሪዎች፣ የማሕበረሰቡ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጥረት ውጤት ነው። በጋር ጠንክሮ ከተሠራ ሁሉም ሊሳካ እንደሚችል ማሳያ ነው” ሲሉ የኬፕ ቨርድ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ፊሎሚና ጎንሳልቬስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ሠራተኛ የሆኑት ዶክተር ዶሮቲ አቹ ፎሳህ ደግሞ መሥሪያ ቤታቸው በውጤቱ “እጅግ እንደተደሰተ” ገልጠዋል።

የጤና ሙያተኞች የኬፕ ቨርድ ውጤት ለሌሎች አነስተኛ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ነው ይላሉ።

በአንድ ወቅት በዘጠኙም የኬፕ ቨርድ አውራጃዎች የወባ በሽታ ተመዝግቦ ነበር።

ዘንድሮ ግን ሳኦ ቲያጎ በተሰኘችው አውራጃ ብቻ ሊገኝ የሚችል ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በሽታው የታየውም በዚህ ሥፍራ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅቷ ዶሮቲ ሀገሪቱ ከዋናው የአፍሪካ ምድር ተገንጥላ ያለች መሆኗ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው አይክዱም።

በመሬት ከተከበበ ሀገር ይልቅ ደሴቶች ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላው በሽታ እንዴት እንደሚስፋፋ ለማስተዋል ይቻላቸዋል።

እንደ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ባሉ በሽታው በተስፋፋባቸው ሀገራት ያሉ ዜጎች ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላኛው ስለሚጓጓዙ በሽታውን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት እጅግ አዳጋች ነው።

ሞውሪሺየስ በአውሮፓውያኑ 1973 ከወባ በሽታ ነፃ የሆነች አፍሪካዊት ሀገር ስትሆን አልጄሪያ ደግሞ በ2019 ይህን ስኬት መጎናፀፍ ችላለች።