ሰልፍ

13 ጥር 2024

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በየመን በሚገኙ የሁቲ አማጺያን ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ ካከሄዱ በኋላ በሰነዓ በሺዎቹ የሚቆጠሩ ድብደባውን አውግዘው አደባባይ ወጡ።

የሁቲ ቃል አቀባይ የአሜሪካ እና የዩኬ የአየር ድብደባን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ አገራቱ ለተግባራቸው “ትልቅ ዋጋን ይከፍላሉ” ብለዋል።

ሁለቱ አገራት በአማጺ ቡድኑ ላይ ጥቃት የፈጸሙት አማጽያኑ በቀይ ባሕር ላይ በመርከቦች ላይ ላደረሱት ጥቃት ምላሽ እንዲሆን ነው ብለዋል።

ኔዘርላንድስ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ባሕሬን ለዚህ ጥቃት ድጋፍ መስጠታቸው ተገልጿል።

እስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ በይፋ አጋርነታቸውን ለሐማስ የገለጹት የሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ሲመቱ ቆይተዋል።

በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ምንም እንኳ በአሜሪካ እና ዩኬ ጥምር ኃይል የአየር ድብደባ ቢፈጸምባቸውም በቀይ ባሕር በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራችንን አናቆምም ብለዋል።

ከሐሙስ ምሽት እስከ አርብ ንጋት ድረስ ከአየር እና ከባሕር 16 የሁቲ ይዞታዎች መደብደባቸውን አሜሪካ አስታውቃለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ዓለም አቀፍ የመርከብ ንግድ እንቅስቃሴን ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው ጥቃቱ “ውስን፣ አስፈላጊና ራስን ለመከላከል የተፈጸመ ተመጣጣኝ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ኔዘርላንድስ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ባሕሬን ለዚህ ጥቃት ድጋፍ መስጠታቸው ተገልጿል

ኢራን፣ ሩሲያ እና ቱርክ ደግሞ በሁቲ አማጺያን የተወሰደውን ወታደራዊ እርምጃ ተችተዋል። የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ወታደራዊ ዘመቻውን ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ነው ብለውታል።

የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ደግሞ ወታደራዊ እርምጃው ሕጋዊ አይደለም ብለዋል። ቃል አቀባዩ “ከዓለም አቀፍ ሕጎች አንጻር ሕጋዊ አይደለም” ካሉ በኋላ የሁቲ አማጺያን መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የሁቲ መሪ ሞሐመድ አል-ቡካቲ፣ አሜሪካ እና ዩኬ “በቅርቡ በታሪካቸው ትልቅ ስህተት መሥራታቸውን ይገነዘባሉ” ብሏል።

የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ደግሞ አሜሪካ እና ዩኬ በጠቅላላው 73 ጊዜ መተኮሳቸውን ገልጸው በጥምር ጦሩ ጥቃት 5 የሁቲ አባላት መገደላቸውን እና 6 መቁሰላቸውን ተናግረዋል።