አንቶኒ

13 ጥር 2024

የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ በከፍተኛ የዝውውር ዋጋ ክለቡን የተቀላቀለው አንቶኒ ብቃቱ የወረደው በሜዳ ውጪ በግል ሕይወቱ ባለ ጉዳይ ነው አሉ።

ብራዚላዊው የክንፍ ተጫዋች የተለያዩ ሦስት ሴቶች አካላዊ ጥቃት ፈጽሞብናል ካሉ በኋላ በፖሊስ ምርመራ ሲደረግበት ቆይቷል።

ተጫዋቹ ምርመራ ይደረግበት እንጂ በብራዚልም ሆነ በዩናይትድ ኪንግደም በቁጥጥር ስር አልዋለም፤ ክስም አልተመሰረተበትም።

ይሁን እንጂ ጥቃት አድርሷል በሚል በቀድሞ ፍቅረኛው ክስ መቅረቡን ተከትሎ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ለጊዜው ታግዶ ነበር።

የሚቀርቡበትን ክሶች ሲያስተባብል የነበረው አንቶኒ በዚህ የውድድር ዓመት ባደረጋቸው 21 ጨዋታዎች በአንዱም ግብ አላስቆጠረም እንዲሁም ለግብ የሚሆን ኳስ አላቀበለም።

“ይመስለኛል ከሜዳ ውጪ ያሉ ጉዳዮች እንዳይጫወት አድርጎታል” ብለዋል አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ።

“ተጽእኖ አሳድረውበታል፤ ይወጣዋል። . . . የተሻለ ነገር እንዲያደርግ የሚፈልገውን ድጋፍ ሁሉ እናደርግለታለን” ብለዋል።

የ23 ዓመቱ አንቶኒ ከአያክስ በ82 ሚሊዮን ፓዎንድ ወደ ዩናይትድ ሲዘዋወር በክለቡ ታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ዋጋ የወጣበት ተጫዋች ሆኖ ነበር።

አንቶኒ ለቀድሞ ክለቡ 82 ጊዜ ተሰልፎ 24 ጎሎችን አስቆጥሮ 22 ኳሶችን ደግሞ ለግብ እንዲሆኑ አመቻችቶ አቀብሏል።

ባለፈው 2022-23 የውድድር ዓመት አንቶኒ 47 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቶ ማስቆጠር የቻለው 10 ግብ ሲሆን ለጎል አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ 5 ብቻ ነው።

አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ “በመጀመሪያው ዓመት ጥሩ ነበር። ከሊጉ መጀመር በፊት በነበሩ ጨዋታዎች በጣም ጥሩ ነበር፣ ሊጉም ከተጀመረ በኋላ ጥሩ ነበር” ካሉ በኋላ፤ ክሱ ይቀርብበት ከጀመረ በኋላ “የሚጠበቅበትን መወጣት አልቻለም። የተሻለ ነገር ማድረግ እንደሚችል እንጠብቃለን” ብለዋል።

በተመሳሳይ የማንቸስተር ዩናይትድ የክንፍ መስመር ተጫዋች የሆነው እንግሊዛዊው ሜሰን ግሪንውድ የቀድሞው ፍቅረኛው ላይ ጥቃት ፈፅሟል ተብሎ ክለቡ ለስድስት ወራት ምርመራ ካደረገ በኋላ ከተጫዋቹ ጋር ለመለያየት መስማማቱ ይታወሳል።

ግሪንውድ በአሁኑ ወቅት በስፔን ለጌታፌ እየተጫወተ ይገኛል።