ታዳጊዎቹ ከአምቡላንስ ሠራተኛ ጋር

13 ጥር 2024, 12:31 EAT

በእንግሊዝ ማዋኛ ገንዳ ውስጥ እራሱን ስቶ ሊሰጥም የነበረን ታናሽ ወንድማቸውን የታደጉት ሁለት እህቶች እውቅና ተሰጣችው።

ሎቪ እና ዶሊ የተባሉት የ7 እና የ9 ዓመት ታዳጊ ሴቶች ጥሎ የሚያንዘረዝር ሕመም ያለበት ታናሽ ወንድማቸው ሬጂ በመዋኛ ገንዳ ውስጥ እራሱን ከሳተ በኋላ ነው በፍጥነት ከውሃ ውስጥ አውጥተውት ሕይወቱን የታደጉት።

እህትማማቾቹ በፍጥነት በወሰዱት እርምጃ ሕይወት በማዳናቸው ከምስራቅ እንግሊዝ የአምቡላንስ አገልግሎት የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

የድንገተኛ አደጋ ሠራተኛ ጆን ግሪምውድ ልጁ በአሁኑ ወቅት በሕይወት ያላው ሁለቱ ታዳጊዎች በወሰዱት ፈጣን እርምጃ ነው ብሏል።

ክስተቱ ሲያጋጥም እናት ባለችበት ሦስቱ ልጆች በመኖሪያ ግቢያቸው በሚገኝ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ እየተጫወቱ ነበር።

የልጆቹ እናት ጄሲካ “ልጆቼ ዋና ይችላሉ። የመዋኛ ገንዳው ጥልቀትም እስከ ወገባቸው ድረስ ብቻ ነው። ስለዚህ የቤት ውስጥ ስራ እየሰራው እየተከታተልኳቸው ነበር” ብላለች።

“ድንገት ትልቋ ልጄ ስትጮኅ ሰማሁ። በሕይወት የሌላ የሚመስለውን ሰውነቱን ተሸክመው አየዋቸው። ሕመሙ ድንገት ተነስቶበት አፉን እንደከፈተ ሰጥሞ ነበር። ትልቋ ልጄ ጭንቅላቱን፤ ትንሿ ደግሞ እግሩን ይዘው በፍጥነት ከውሃ ውስጥ አወጡት” በማለት የተከሰተውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ጥሪ የደረሰው የአምቡላንስ አገልግሎትም የመጀመሪያ እርዳታ በቦታው አድርጎ ልጁን ወደ ሆስፒታል ከወሰደው በኋላ ታዳጊው ሙሉ በሙሉ ደህና ሆኗል።

የልጆቹ እናት ጄሲካ ስትናገር “ሎዊ እና ዶሊ ጥቂት ሴኮንዶችን ዘግይተው ቢሆን የልጄ ሕይወት ያልፍ ነበር። በልጆቼ ተግባር እጅጉን ኮርቻለሁ” ብላለች።

የአምቡላንስ አግልግሎትም ለተግባራቸው እውቅና እንዲሆን በትምህርት ቤታቸው ተገኝቶ ሰርተፊኬት አበርክቶላቸዋል።