ታጋቾች ነጻ እንዲወጡ ሲጠየቅ

13 ጥር 2024, 08:56 EAT

በጋዛ በሐማስ ታግተው ላሉ እስራኤላውያን መድኃኒት ሊደርስ መሆኑ ተገለጸ።

አዲስ በተደረሰ ስምምነት መሠረት ለእስራኤላውያን ታጋቾች በጋዛ መድኃኒት እንደሚሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናግረዋል።

የታጋቾች ቤተሰቦች ካታር ሄደው ለአሸማጋዮች መድኃኒት ወደ ጋዛ እንዲገባ ከጠየቁ በኋላ ነው ስምምነቱ የተደረሰው።

መድኃኒት ገና መውሰድ አልተጀመረም። በምን መንገድ እንደሚጓጓዝም ግልጽ አይደለም።

በጋዛ በሕይወት ያሉት 105 ታጋቾች መሆናቸው ይታመናል።

በሐማስ ተወስደው የነበሩት 240 ታጋቾች ሲሆኑ፣ የተኩስ አቁም በነበረ ወቅት 105 ሰዎች ተለቀዋል። 25 ታጋቾች እንደሞቱ ይታመናል።

ሐማስ እንዲሁም እስራኤልም መድኃኒቶቹ እንዲጓጓዙ ፈቃደኛነት አሳይተዋል።

አሸማጋዮች ከሁለቱም ወገኖች ጋር በመነጋገር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የተራድኦ ተቋማት ጋር የትኞቹ መድኃኒቶች እንደሚያስፈልጉ በመምከር እየሠሩ መሆኑ ተገልጿል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት በቀጣይ ጥቂት ቀናት መድኃኒቶች ይደርሳሉ።

የፍልስጤማ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ወደ ጋዛ መድኃኒት ለመውሰድ ውይይቶች ተካሂደዋል።

የታጋቾች ቤተሰቦች እንደሚሉት መድኃኒት በማጣት ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ ታጋቾች አሉ።

ቀድሞ ሕመም የነበረበባቸው ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑም ገልጸዋል።

1,300 እስራኤላውያን ሲገደሉ 240 በሐማስ ታግተው ተወስደዋል።

በእስራኤል ጥቃት በአብዛኛዎቹ ሴቶችና ሕጻናት የሆኑ 23,350 ሰዎች እስካሁን ተገድለዋል።