ሪያድ ማሕሬዝ እና ሌሎችም ተጫዋቾች የሚታዩበት ምስል

14 ጥር 2024, 08:18 EAT

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ቅዳሜ ተጀምሯል። በመክፈቻው ጨዋታ አስተናጋጇ አይቮሪኮስት ከጊኒ ቢሳው ጋር ተጫውታለች።

የሳዲዮ ማኔዋ ሴኔጋል ወደ ውድድሩ የምታመራው ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን በመሆን ነው። ዘንድሮስ የማሸነፍ ዕድላቸው ምን ያህል ነው?

ቢቢሲ ስፖርት ከኦፕታ ጋር በመተባበር ማን የአፍሪካ ሻምፒዮን ሊሆን እንደሚችል ለማየት ሞክሯል።

ኦፕታ ስፖርታዊ አሃዞችን የሚተነትን ተቋም ነው።

የዋንጫ ባለቤቷ ሴኔጋል፣ የዓለም ዋንጫዋ አስገራሚ ቡድን ሞሮኮ ወይስ በርካታ ጎሎችን በማስቆተር ላይ የምትገኘው ናይጄሪያ የማሸነፍ ዕድል አላቸው?

የኦፕታን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የትንበያ ሞዴልን በመጠቀም ሴኔጋል ዋንጫውን በድጋሚ ለማንሳት ዕድል አላት። በተከታታይ ዋንጫውን በማንሳትም አራተኛዋ ቡድን ትሆናለች።

ከ2006 እስከ 2010 ግብጽ ለተከታታይ ሦስት ጊዜ ባለድል ከሆነች በኋላም የመጀመሪያዋ ቡድን ትሆናለች። ያለፉት 6 የዋንጫው አሸናፊዎች አንዳቸውም ከ16 ቱ ማለፍ አልቻሉም።

የአፍሪካ ዋንጫውን ማን እንደሚያሸንፍ የበለጠ የተሟላ ስዕል ለማግኘት የትንበያ ሞዴሉ የእያንዳንዱን ጨዋታ ገምቷል። የውርርድ ዕድሎችን እና የኦፕታን የብሔራዊ ቡድን ደረጃዎችንም ተጠቅሟል።

ግምቱ እና ደረጃው በታሪካዊ እና የቅርብ ጊዜ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ የተመሰረተ ነው። ሞዴሉ የተጋጣሚን ጥንካሬን እና ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ አስቸጋሪነት ተመልክቷል። ለዚህም የጨዋታ ግምቶችን፣ የቡድኖቹን ስብጥር እና የማለፍ ደረጃ ተጠቅሟል።

በዚህ ሞዴል መሠረት ሴኔጋል 12.8 በመቶ ማሸነፍ ዕድል አግኝታለች። ከ1992 እና 2015 በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫው ለማንሳት የምትሞክረው አስተናጋጇ አይቮሪኮስት (12.1 በመቶ) ተከታዩን ቦታ ይዛለች።

ውድድሩን በማዘጋጀት ዋንጫውን ያነሳችው የመጨረሻዋ ቡድን ግብጽ ስትሆን ጊዜውም እአአ በ2006 ነበር። ካለፉት 9 ውድድሮች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡት ጋና እና ካሜሮን ሲሆኑ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ሞሮኮ (11.1 በመቶ) ውድድሩን የማሸነፍ ሦስተኛውን ምርጥ ዕድል በሞዴሉ ተሰጥቷታል። እአአ በ1976 ካሸነፉ በኋላ ሁለተኛውን የአፍሪካ ዋንጫቸውን ለማንሳት ያልማሉ። በ2004 የፍፃሜ ጨዋታ በቱኒዚያ 2 ለ 1 ከተሸነፉ በኋላ በተሳተፉባቸው 7 ውድድሮች ሩብ ፍፃሜውን ማለፍ አልቻሉም።

የማሸነፍ ተስፋ ካላቸው አገራት አልጄሪያ (9.7 በመቶ) በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ግብጽ አምስተኛ (8.5 በመቶ) ሆናለች። ለአልጄሪያ የማሸነፍ ዕድሏ ከሌሎቹ ቡድኖች በበለጠ ጥሩ የሆነላት ቀላል ምድብ ውስጥ በመገኘቷ ነው።

ሰባት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ክብረ ወሰን የያዘችው ግብጽ በ2021 የፍጻሜ ጨዋታ በሴኔጋል በፍፁም ቅጣት ምት በመሸነፏ ያጋጠማትን ሃዘን ትበቀል ይሆን? ማሳካት ከቻለች ከ2010 ወዲህ የመጀመሪያው ዋንጫዋ ይሆናል።

ሞሃመድ ሳላህ በ 2017 የፍጻሜ ጨዋታ ሽንፈትን በማስተናገዱ ከሁለት የፍጻሜ ስንፈት በኋላ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማንሳት ይጓጓል። መልካሙ ዜና ግብጽ ዘንድሮ ለፍፃሜ ለመድረስ 16 በመቶ ዕድል አላት።

በኦፕታ ትንበያ መሠረት ዋንጫውን ለማንሳት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ሰባቱ ምርጥ ቡድኖች ውስት የሦስት ጊዜ አሸናፊዋ ናይጄሪያ (1980፣ 1994 እና 2013) እና የአምስት ጊዜ ሻምፒዮናዋ ካሜሩን (1984፣ 1988፣ 2000፣ 2002 እና 2017) ተካተውበታል። ናይጄሪያ 8.1 በመቶ ዋንጫ የማንሳት ዕድሏሲኖራት ካሜሩን ደግሞ 7.5 በመቶ ዕድል አላት።

በአጉሪቱ እግር ኳስ ስመ ገናና ሆኑት ሁለቱ አገራት ጠንካራ ጎል አስቆጣሪዎች አሏቸው። የ2023 የአፍሪካ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የሆነው ቪክቶር ኦሲምሄ በምድብ ማጣሪያው ለናይጄሪያ 10 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል። ይህም ከሌሎቹ ተጫዋቾች በአምስት ብልጫ አለው። በምድብ ማጣሪያው ብሔራዊ ቡድኑ በአጠቃላይ 22 ጎሎችን አስቆጥሯል።

የካሜሩኑ አምበል ቪንሴንት አቡባከር በ 2021 ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር የወርቅ ጫማ ያሸነፈበትን ብቃቱን ለመድገም ያልማል። በ1974 የአፍሪካ ዋንጫ 9 ጎሎችን ያስቆጠረው የዛየሩ ንዳዬ ሙላምባ በአንድ ውድድር በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

ሴኔጋል በ2021 እንዳደረገችው የመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ የሚያደርግ ቡድን ይኖር ይሆን? እንደዚያ ከሆነ ማሊ (3.7 በመቶ) ጥሩ ዕድል ያላት ይመስላል። በአውሮፓ 5ቱ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ 12 ተጨዋቾችን የሚያሳትፉት ንስሮቹ በ1972 ሁለተኛ ሆነው ካጠናቀቁበት ውድድር በኋላ ለፍጻሜ የመድረስ 8.7 በመቶ ዕድል አላቸው።

5.4 በመቶ የሆነ ጠባብ ነጥብ ብቻ የሰባት ቡድኖችን የማሸነፍ ዕድል በለየበት የአፍሪካ ዋንጫ ክፍት እና አስደሳች ውድድር እንደሚሆን ይጠበቃል። ብቻ ይገባዋል የተባለው ቡድን የሚሸሰንፍበት ውድድር እንዲሆን ተስፋ እናድርግ።