ጆ ባይደን

ከ 7 ሰአት በፊት

ፕሬዝዳንት ባይደን ሁቲዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘራችን ለኢራን በግል የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲደርሳት አድርጋናል አሉ።

ጆ ባይደን ይህን ያሉት አሜሪካ በሁቲ የጦር ቀጠና ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የአየር ጥቃት ካደረሰች በኋላ ነው።

ኢራን፤ ሁቲዎች በቀይ ባሕር አካባቢ የሚሰነዝሩት ጥቃት ላይ እጄ የለበትም ትላለች።

ይሁንና ምእራባዊያን እንደሚያምኑት ቴህራን ለሁቲዎች አስፈላጊ መሣሪያዎችን ታቀርባለች።

አሜሪካ እንደምትለው ደግሞ የኢራን ቴክኖሎጂ ድጋፍ ባይኖር ሁቲዎች መርከቦችን ነጥሎ ለመምታት የሚያስችል አቅም አይኖራቸውም።

ዩኬና አሜሪካ በተቀናጁበት የአየር ጥቃት 30 የሚሆኑ የሁቲ ወታደራዊ የስበት መእከላት ኢላማ ተደርገዋል። በዚህ ጥቃት ካናዳና አውስትራሊያ ድጋፍ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ማእከላዊ እዝ እንዳለው ቶማሃውክ የመሬት ክሩዝ ሚሳኤልን በመጠቀም ነው በሁቲ ጠቃሚ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ያደረስነው ሲል አስታውቋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ብሪቴይን ይህን ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ሌላ አማራጭ አላገኘችም ብለዋል።

ሁቲዎች በቀይ ባሕር በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ለፍልስጤም ሕዝብ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ነበር።

ቴሌግራፍ ላይ ዴቪድ ካሜሮን ባሳተሙት ጽሑፍ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከአሜሪካ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው በተመረጡ ዒላማዎች በሁቲ ላይ የተመጠነ ጥቃት ለመሰንዘር ተስማምተዋል ብለዋል።

የሁቲ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ እንዳሉት ደግሞ የተሰነዘሩት ጥቃቶች በሠራዊታቸው ላይ ምንም ተጽእኖ የሚያስከትል አይደለም ብለዋል።

ሁቲዎች ከሺአ ሙስሊም አንድ ክፍል ሲሆኑ ዛያዲስ በሚል ይታወቃሉ። ብዙ የመናዊያን በሁቲ ቁጥጥር ሥር በሆኑ አካባቢዎች ነው የሚኖሩት። ዋና ከተማዋን ሰንአን ጨምሮ የቀይ ባሕር ጠረፎችን የሚቆጣጠሩትም ሁቲዎች ናቸው።

የምዕራባዊያን ይፋ የሆነው አመለካከት ሁቲዎች ከጋዛ ጦርነት ጋር ምንም የሚያይዛቸው ነገር እንደሌለ የሚያሳይ ነው። ጥቃት እንዲሰነዘርባቸው የሆነውም የንግድ መርከቦች ላይ ዒላማ ያደረገ ጥቃት እየሰነዘሩ ስለሆነ ነው።

ነገር ግን በየመንና በተቀረው ዓለም የአሜሪካና ዩኬ በሁቲ ላይ የሰነዘሩት ጥቃት የሚታየው ለእስራኤል ድጋፍ እንደመስጠት ተደርጎ ነው።

ብዙዎች አሜሪካና ዩኬ ከእስራኤል ጎን ተሰልፈው ጋዛን እያጠቁ እንደሆነ ነው የሚያምኑት።

አሜሪካና ዩኬ ከሰሞኑ የሰነዘሩት ጥቃት በሁቲዎች ላይ ከፍተኛ መሽመድመድ እንዲደርስባቸው ሊያደርግ የሚችል ነው።

ይሁንና በአሜሪካና ዩኬ የመን ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች ቀጣይነት ካላቸው ምናልባት ሁለቱ አገራት ለተራዘመ ጦርነት ይጋለጣሉ የሚል ስጋት አለ።

ሳኡዲ በየመን ጦርነት እጇን ካስገባች ወዲህ ለስምንት ዓመታት ጥቃት ብትሰነዝርም ሁቲዎችን ለማጥፋት ሳትችል ቀርታለች።

የዓለም 15% የንግድ መርከቦች መተላለፊያ የሆነው ቀይ ባሕር በሁቲዎች ተደጋጋሚ ጥቃት የተነሳ ሰላም ርቆታል።

በርካታ ግዙፍ የሚባሉ የመርከብ ኩባንያዎችም ጉዟቸውን ከቀይ ባሕር ለማራቅ ተገደዋል።