ቦሪስ አኩኒን የተሰኘው የልብ-ወለድ መፃሕፍት ደራሲ

ከ 9 ሰአት በፊት

ሩሲያ ቦሪስ አኩኒን የተሰኘው የሀገሪቱ ጉምቱ የልብ-ወለድ መፃሕፍት ደራሲ “የውጭ ተላላኪ” ነው ስትል ፈረጀች።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት አጥብቆ የሚቃወመው አኩኒን በሀገሪቱ ፍትሕ ሚኒስቴር “አሸባሪዎችና አክራሪዎች” መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሯል።

የ67 ዓመቱ ደራሲ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን አጥብቆ በመተቸት ይታወቃል።

ከጦርነቱ በፊት የደራሲው ሥራ የሆነው የአንድ መርማሪ ፖሊስን ሕይወት የሚዳስስ መፅሐፍ በሩሲያ እጅግ ዝናው ገኖ ነበር።

ነገር ግን ባለሥልጣናት መፅሐፉ እንዳይሸጥ እግድ ጥለዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለው ፤ ግሪጎሪ ችካርቲሽቪል በተሰኘ የመዝገብ ስሙ የሚታወቀው አኩኒን “በሩሲያ የሚካሄደውን ልኡ ኦፕሬሽን ተቃውሟል።”

ሚኒስቴሩ አክሎ ደራሲው “የሩሲያን ስም የሚያጎድፍ ሐሰተኛ መረጃ አስፋፍቷል” ሲል ይከሳል።

ደራሲው ከዚህ አልፎ የዩክሬንን ወታደራዊ አቅም ለማደራጀት ያለመ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ ሠርቷል በሚል ተከሷል።

ሩሲያ በሙሉ ኃይሏ ዩክሬንን በወረረች ቀን ደራሲው እንዲህ ሲል ፅፎ ነበር፡ “ሩሲያ የምትመራው የሥነ-ልቡና ቀውስ ባለበት ጠቅላይ ገዥ ነው። ከዚህም ብሶ የሚያስጨንቀውን ነገር የሚሰማ ሰው ነው።”

አሁን ነዋሪነቱን ለንደን ያደረገው ደራሲው አኩኒን አርብ ዕለት በሽብርተኝነት መፈረጁን ሲሰማ “አሸባሪዎች አሸባሪ ነህ አሉኝ” ሲል ፅፏል።

“የውጭ ተላላኪ” የተሰኘው ቃል በሶቪየት ዘመን “የሕዝብ ጠላት” ከሚለው ፍረጃ ጋር ተመሳሳይነት አለው።

ይህ ስያሜ የተሰጣቸው ሰዎች በማሕበራዊ ሚድያም ሆነ በሌሎች ገፆች ራሳቸውን “የውጭ ተላላኪ” ብለው እንዲሰይሙ ይጠይቃል።

ከዚህ አልፎ ይህ ስም የተሰጣቸው ግለሰቦች ስለገንዘብ አጠቃቀማቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።

በርካታ ታዋቂ ሩሲያዊያን ፑቲን ዩክሬንን በወረረች ወቅት ሀገራቸውን ጥለው ወጥተዋል።

ሀገር ቤት ያሉት ደግሞ ጥብቅ የሆነ ክትትል እና ሳንሱር ይደርግባቸዋል።