ጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ

ከ 9 ሰአት በፊት

ታዋቂው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ አስፋው መሸሻ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ለበርካታ ዓመታት የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ፕሮግራሞችን በማቅረብ የሚታወቀው አስፋው ባደረበት ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል።

ጋዜጠኛው ይሰራበት የነበረው ኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ወንድማችንና የሥራ ባልደረባችን አስፋው መሸሻ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል” ሲል በፌስቡክ ገፁ አስነብቧል።

ጣቢያ አክሎ ጋዜጠኛ አስፋው፤ ባደረበት ህመም በህክምና ሲታገዝ እንደቆየ አስታውሷል።

አስፋው መሸሻ በተለይ በቅርብ ዓመታት “ኑሮን በአሜሪካ” እንዲሁም “እሑድን በኢቢኤስ” በተሰኙ ፕሮግራሞቹ በርካታ ተከታዮች አፍርቷል።

የራድዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ሆኖ ያገለገለው አስፋው መሸሻ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የጤና እክል እንደገጠመው ይታወሳል።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛው የሕክምና አልግሎት ለማግኘት ባቀናበት ዩናይትድ ስቴትስ ሕይወቱ እንዳለፈ አስነብበዋል።

አስፋው፤ ለረዥም ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካ አድርጎ ከቆየ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢነት ሲያገለግል ቆይቷል።

ፕሮግራም ማዘጋጀት እና ማቅረብ ከ20 ዓመት በፊት በሬዲዮ የጀመረው አስፋው፤ በአገሪቱ ቀዳሚ በሚባለው ኤፍኤም እዲስ 97.1 ላይ የሙዚቃ ፕሮግራም አቅራቢ ነበር::

‘አይሬ’ በመባል ይታወቅ የነበረውን ተወዳጅ የሙዚቃ ፕሮግራም በማቅረብ ለዓመታት ቆይቶ፤ ወደ ቴሌቪዝን በመምጣት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ የእሁድ መዝናኛ ላይ ለዓመታት በአዘጋጅነት እና በአቅራቢነት በመሳተፍ በበርካቶች ተወዳጅ ለመሆን ችሏል::