አዲሱ የታይዋን ፕሬዝዳንት ሚስተር 'ላይ'
የምስሉ መግለጫ,አዲሱ የታይዋን ፕሬዝዳንት ሚስተር ‘ላይ’

14 ጥር 2024, 10:08 EAT

ተሻሽሏል ከ 8 ሰአት በፊት

በሙያቸው ሐኪም የሆኑትና ለቻይና አንንበረከክም በማለታቸው የሚታወቁት ዊሊያም ላይ የታይዋንን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸነፉ።

ቤጂንግ እኚህን ግለሰብ ‘አስቸጋሪና አደገኛ’ ብላ ነው የምትጠራቸው።

ላይ ለሚቀጥሉት ዓመታት የታይዋን ፕሬዝዳንት ሆነው ይሠራሉ።

ቻይና ታይዋን ደሴትን አንድ አካሏ አድርጋ ነው አሁንም የምትመለከታት።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ለማሳካት ከሚሹት ነገር አንዱ ታይዋንን ወደ ቻይና መመለስ ነው።

ቻይና ከታይዋን ምርጫ በፊት የታይዋን ሕዝብ ለዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ወይም በምሕጻሩ ዲፒፒ ድምጽ እንዳይሰጡ አሳስባ ነበር።

ዲፒፒ ገዢው የታይዋን ፓርቲ ሲሆን የዚሁ ፓርቲ አባል የሆኑት የ64 ዓመቱ የሕክምና ዶክተሩ ዊሊያም ላይ ቺንግ አሸናፊ ሆነዋል።

ፕሬዝዳንት ላይ ከቻይና ጋር አንድ ሁለት በመባባል የሚታወቁ ፖለቲከኛ ናቸው።

ገዢው ፓርቲ ባልተመለደ ሁኔታ ለሦስተኛ ጊዜ መመረጡ አስገራሚ ሆኗል።

ዲፒፒ ፓርቲን ቻይና አምርራ ትጠላዋለች።

ፕሬዝዳንት ላይ ቀጣዩ የሥልጣን ዘመናቸው ያለፉት 8 ዓመታትን የመሩትን የሳይ ኢንግ ዊን ቀጣይ ምዕራፍ ይሆናል ብለዋል።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕሬዝዳንት ላይ ‘ታይዋን ነጻ አገር መሆኗን ማወጅ አያስፈልጋትም፣ ምክንያቱም ታይዋን ሉአላዊና ነጻ አገር ስለሆነች’ ሲሉ ነበር።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ይህን ይበሉ እንጂ ደጋፊዎቻቸው ለርሳቸው ድምጽ ሲሰጡ የታይዋንን ነጻ አገርነት ያውጃሉ ወደ አዲስ ምዕራፍን ይወስዱታል በሚል ነው።

ሚስተር ላይም ሆነ አጋራቸው ቢ ኪም በቻይና ፍጹም የሚጠሉ ሰዎች ሲሆኑ ወደ ቻይናም ሆነ ሆንግ ኮንግ እንዳይገቡ እግድ ተጥሎባቸዋል።

በዚህ የተነሳ ቻይና ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር ንግግር ይኖራታል ተብሎ አይጠበቅም።

ታይዋንና ቻይና ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ቀጥታ ንግግር ኖሯቸው አያውቅም።

ቻይና ቀጥታ ንግግሩን ያቋረጠችው የቀድሞው የታይዋን ፕሬዝዳንት ግዛታቸው ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን በይፋ እንዲገልጹ ተጠይቀው አሻፈረኝ ካሉ በኋላ ነው።

ቻይና ለታይዋን እውቅና የሰጡ አገሮችን በንግድ በማማለል እንዲሁም ተጫማሪ የንግድ ማእቀቦችን በመጣል ታይዋንን የመነጠለክ ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች ተብሎ ይጠበቃል።

አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት በመጪው ጊዜ ባሕር ሠርጓጅ መርከብ ግንባታን እንደሚያጠናክሩ፤ የታይዋንን ወታደራዊ አቅም እንደሚያባዙና ከአሜሪካ፣ ከጃፓንና አውሮፓ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያዳብሩ ቃል ገብተዋል።

ይህ ቻይናን አስቆጥቷል።

የፕሬዝዳንት ላይ መመረጥ አሜሪካንን ጭምር ሳያሳስባት አልቀረም። ምክንያቱም ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ቀጥተኛነትና የታይዋንን ነጻነት ለማወጅ ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸው ከቻይና ጋር ወደ ፍጥጫ ሊከት ይችላል የሚል ስጋት ነው።

የገዥው ፓርቲ ተቀናቃኝ የነበረውና በዚህ ምርጫ ድል ያልቀናው ኬኤምቲ የብዙ ታይዋናዊንን ሥጋት ይዞ ነበር የተነሳው። ይህ ስጋት ደግሞ ይዘገይ ይሆናል እንጂ ቻይና ታይዋን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ትሰነዝራለች የሚል ነው።

ኬኤምቲ ፓርቲ ታይዋን ከቻይና ጋር መልካም ግንኙነት ብትፈጥር ነው ደኅንነቷ ይበልጥ የሚጠበቀው ብሎ ያምናል።