አይቮሪ ኮስት ከጊኒ ቢሳው ሲጫወቱ

ከ 7 ሰአት በፊት

አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት የ2023 የአፍሪካ ዋንጫን በድል ጀምራለች።

ዝሆኖቹ በደጋፊያቸው ፊት ጊኒ ቢሳውን 2 ለምንም በመርታት የዘንድሮውን ውድድር አሐዱ ብለው ጀምረዋል።

ሴኮ ፎፋና በአራተኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳንዱቅ ውስጥ አሳምሮ ወደ መረባ የሰደዳት ኳስ ለአስተናጋጆቹ መሪነትን አጎናፅፋለች።

ዣን-ፊሊፕ ክራሶ ደግሞ ከእረፍት በኋላ ሁለተኛዋን ጎል በማስቆጠር ሀገሩን ባለድል አድርጓል።

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በዝናብ ወቅት ምክንያት መካሄድ ከነበረበት ስድስት ወራት ዘግይቶ ነው እየተካሄደ ያለው።

ነገር ግን መዘግየቱ ለዝግጅቱ 1 ቢሊዮን ዶላር ላወጣችው አይቮሪ ኮስት መልካም ዜና ሆኗል።

የአፍሪካ ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ለማንሳት የሚያልሙት አስተናጋጆቹ የመጀመሪያውን ምድብ መምራት ጀምረዋል።

ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 1992 እና 2015 የአህጉሪቱን ጉምቱ የእግር ኳስ ውድድር ማሸነፍ ችለዋል።

የአይቮሪ ኮስት ቀዳም ምርጫ የሆነው ሴባስቺያን አለር በጉዳት ምክንያት ባይሰለፍም ዝሆኖቹ ድል ከማድረግ ወደኋላ አላሉም።

አማካዮቹ ፎፋና እና ፍራንክ ኬሲዬ ተቀናጅተው ደጋፊያቸውን ገና በጨዋታው መባቻ አስፈንድቀዋል።

የጊኒ ቢሳው አጥቂ ማማ ባልዴ ለጎል የቀረበ ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬም የሚቀጥሉ ሲሆን ከሰዓት 11፡00 ናይጄሪያ ከኢኳቶሪያ ጊኒ ይጫወታሉ።

ምሽት 2፡00 ግብፅ ከሞዛምቢክ፤ 5፡00 ደግሞ ጋና ከኬፕ ቨርድ ይፋለማሉ።

የአይቮሪ ኮስት መንግሥት ይህ ውድድር በአገሪቱ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በ2011 ካበቃ በኋላ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ያስመዘገበችውን አስደናቂ ለውጥ እንደሚያፋጥነው ተስፋ ሰንቋል።

ውድድሩን ለማዘጋጀት የአገሪቱ መንግሥት ቢያንስ 1 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ አድርጓል። አራት አዳዲስ ስታዲየሞች ተገንብተዋል። ሁለቱ ደግሞ ትልቅ እድሳት ተደርጎላቸዋል።

ጨዋታዎቹን የሚያስተናግዱት አምስት ከተሞች አቢጃን፣ ቡዋኬ፣ ኮርሆጎ፣ ሳን ፔድሮ እና ዋና ከተማዋ ያሙሶክሮ ናቸው።

አይቮሪ ኮስት በእነዚህ ከተሞች የአየር ማረፊያዎች፣ መንገዶች፣ ሆስፒታሎችና ሆቴሎች ገንብታለች አልያም ማሻሻያ አድርጋለች።