ዳይመንድ

ከ 6 ሰአት በፊት

እአአ በ2017 ከሴራሊዮን ጥሩ ዜና ተሰማ።

በአገሪቱ የተገኘው አልማዝ ነበር የዓለም መገናኛ ብዙኃንን የተቆጣጠረው።

በሴራሊዮን አልማዝ የሚለው ቃል ከስቃይና ደም መፋሰስ ጋር የተሳሰረ ነው።

‘peace diamond’ የተባለው ይህ አልማዝ ተሽጦ የአገሬውን ሰው ሕይወት ይለውጣል የሚል ተስፋ ነበር።

ከዜናው ጀርባ ያሉት ጀርባቸው እስኪጎብጥ ለፍተው አልማዙን ያገኙት ሠራተኞች ናቸው።

ከአምስቱ ሠራተኞች መካከል ኮምባ ጆንቡል እና አንድሪው ሳፊያ ይገኙበታል። ሁለቱም ገና ታዳጊ ናቸው።

አልማዙ ከአፈር ውስጥ እያንፀባረቀ ሲመለከቱት ሕይወታቸው እንደተለወጠ አመኑ።

ይህ ከሆነ ስድስት ዓመታት አልፈዋል። ዜናውም ደብዝዟል። እንደጠበቁትም አልሆነም።

አንድሪው ሳፊያ ጎበዝ ተማሪ ቢሆንም በድህነት ምክንያት ትምህርት አቋረጠ።

የኮምባ ጆንቡል ቤተሰብ ከ1991-2002 በነበረው የሴራሊዮን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳልነበር ሆኗል።

ከሌሎች አምስት ቆፋሪዎች ጋር ሆነው ነው ሥራ የጀመሩት። ቀጣሪያቸው በአካባቢው ያለ ፓስተር ነበር።

ደመወዝ ባይኖራቸውም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መሠረታዊ አገልግሎት ያገኛሉ።

አልማዝ ከተገኘ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ቀጣሪው ነው።

ታዳጊዎቹ የሚሠሩበትን ሰዓት ተከፋፈሉ። ከንጋት እስከ ቀትር ከዚያም እስከ ቀኑ መገባደጃ ድረስ።

ገንዘብ አጠራቅመው ትምህር ቤት መመለስ ነበር ሕልማቸው። ሥራው አታካች ነበር።

“ሕልሜ መቀጨቱን ለጓደኛዬ ነገርኩት” ይላል ታዳጊው።

ሙቀት ሲበረታ ለመሥራት ይፈትን ነበር። ዝናብ ሲመጣም እንዲሁ።

“ራሳችንን እናበረታታ፣ እናጽናና ነበር። እንቀልድም ነበር። ሙዚቃ በብሊቱዝ ከፍተን እንሰማም ነበር” ሲል ነው የሚያስታውሰው።

ድንገት ሃብታም ቢሆኑ ምን እንደሚያደርጉ ያሰላስሉ ነበር።

አንድሪው ሳፊያ ትምህርቱን መጨረስ ይመኛል።

የኮምባ ጆንቡል ሁለት ፎቅ ያለው ቤትና ቶዮታ መኪና ይመኛል።

ትልቁ አልማዝ

ትልቁ አልማዝ የተገነበት ቀን ከሌሎች ቀናት የተለየ ነው።

ቁርስ የበሉት ሙዝ ነበር። ፀሎት አድርሰው ወደ ሥራ አቀኑ።

ቆፋሪዎች አልማዝ የሚፈልጉት ለአነስተኛ ጊዜ ነው።

መጋቢት 13/ 2017 ነበር። የዛን ቀን ዕቅዳቸው ማዕድን ማውጫው አቅራቢያ መሥራት ነበር። መንገድ መደልደልን ጨምሮ በዝናባማው ወቅት ጎርፍን መከላከል ነበር ሥራው።

ኮምባ አንፀባራቂ ነገር አየ።

“ውሃ ሥር ነበር ያየሁት። ከዚያ በፊት አልማዝ አይቼ ባላውቅም ልክ ሳየው አልማዝ መሆኑን ቀልቤ ነው የነገረኝ። ከአንድ ደቂቃ በላይ ድንጋዩ ላይ አፈጠጥኩ። ከዚያ አጎቴን እንዲህ አልኩት፣ ‘አጎቴ ያ የሚያንፀባርቀው ምን ያለ ድንጋይ ነው?”

ከውሃው ድንጋዩን አወጣው።

“በጣም ይቀዘቅዝ ነበር። ከዚያ ከእጄ ነጠቁኝና ‘ይሄኮ አልማዝ ነው’ አሉኝ።”

አልማዙ 709 ካራት ነው። በዓለም መዝገብ ከሰፈሩ መካከል 14ኛ ትልቁ አልማዝ ነው።

ቀጣሪያቸውን ደወሉለት። ፓስተር ኢማኑኤል ሞሞህ በቦታው ደረሰ። በጥቁር ገበያ ከመሸጥ ይልቅ ወደ ሴራ ሊዮን መንግሥት ይዞት ሄደ።

በጨረታ 6.5 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴራ ሊዮናውያን በቁፋሮ ነው የሚተዳደሩት። የታዳጊዎቹ ሕይወት እንደሚለወጥም ነበር ያሰቡት።

ብዙዎች ሕልማቸው ትንሽም ቢሆን አልማዝ ማግኘት ነው። እንዲህ ያለ ትልቅ አልማዝ ያገኘ ሰው ሕይወት እስከወዲያኛው እንደሚለወጥ አምነው ነበር።

ቆፋሪዎቹ ከሽያጩ ድርሻ እንደሚያገኙ ተስማምተው ነበር። የተወሰነው ገቢ ደግሞ ለአካባቢው አስተዳደር ይሰጣል።

በመጀመሪያው ዙር እያንዳንዳቸው 80,000 ዶላር አገኙ።

ታዳጊዎቹ ካለሙት በላይ ነበር።

ሆኖም ግን የተሰጣቸው ድርሻ ውስን ነበር።

“ገንዘቡ ሲሰጠኝ ሳልነካው አንድ ሳምንት አስቀመትኩት። ከዚያ ወደ ፍሪታውን ሄጄ ቤት ገዛሁ” ይላል ኮምባ።

አንድሪው ካናዳ ሄዶ ትምህርቱን መቀጠል ነበር ሕልሙ። ኮምባም አብሮት መሄድ ይፈልግ ነበር።

ሆኖም ቪዛ ሳይሰጣቸው ቀረ።

አሁን ኮምባ ገንዘቡ አልቆበታል። አንድሪው ደግሞ ወደ ሌላ አገር ተሰዷል።

ሹፌር ሆኖ ቀን እየሠራ ማታ ማታ እንደሚማር ተነግሮት ነበር የሄደው። እውነታው ግን ይህ አልነበረም።

“ፈረስ እንከባከባለሁ። የምተኛውና የምበላውም እዚ ነው። ሌሎች ሠራተኞች ማረፊያ አላቸው። እኔ ግን የለኝም” ይላል።

አልማዝ ካገኙ በኋላ የጠበቁት ሕይወት ይሄ አልነበረም።

ዕውቅና ማጣት

ሁለቱን ወጣቶች አሁን የበለጠ የሚያሳዝናቸው አልማዙን ለማግኘታቸው ዕውቅና አለማግኘታቸው ነው።

የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ፓስተሩ ላይ ነበር።

ቆፋሪዎቹ ዕውቅና አላገኙም። እንደተረሱና እንደተገፉ ይሰማቸዋል።

አንድሪው ገንዘቡን በሌላ ነገር ላይ ቢያውለው ነበር ምርጫው።

“ያኔ ገና ታዳጊ ነበርኩ። አሁን ላይ ውሳኔዬን ሳስበው ደስተኛ አይደለሁም” ይላል።

“ውጭ አገር የመሄድ ሕልም ባይኖረኝና እዛው አገሬ ብሠራ ይሻል ነበር። ገንዘቤን አባከንኩ” ሲል ያክላል።

አንድሪው ከሳፊያ ጋር ፍሪታውን ለመኖር አስቧል።

ሳፊያ የአልሙንየም መስኮት ንግድ ውስጥ ገብቷል።

“ቤተሰቦቼ ቤት አልነበራቸው” ይላል ሳፊያ።

“አሁን ልጆቼ በአባታቸው ቤት እያደጉ ነው። ለኔ ያ ትልቅ ነበር ነው። ልጆቼ እንደኔ አይሰቃዩም” ሲል ያክላል።