ማዕድን አውጪዎች

ከ 5 ሰአት በፊት

በሰሜናዊ ታንዛኒያ በሚገኝ ሕጋዊ ባልሆነ የማዕድን ማውጫ ላይ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 22 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

አደጋው የደረሰው ቅዳሜ ዕለት በባሪዲ ወረዳ ሲሚዩ ክልል ንጋሊታ ማዕድን ማውጫ ነው ሲሉ የወረዳው ኮሚሽነር ሲሞን ሲማለንጋ ተናግረዋል።

በከባድ ዝናብ ምክንያት ሥራ እንዲቋረጥ በተገደበት አካባቢ የተወሰኑ ሰዎች የማዕድን ማውጣት ከጀመሩ በኋላ ነው አደጋው መድረሱን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን በዜናው “ታላቅ ሃዘንን” እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

“እነዚህ ታንዛኒያውያን ድሃ ማዕድን አውጭዎች ሲሆኑ ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው መተዳደሪያ ለማግኘት ይጥሩ የነበሩ ናቸው” ሲሉ ኤክስ ላይ ጽፈዋል።

በማዕድን ማውጫው ውስጥ ከ19 እስከ 20 ሰዎች አደጋ እንደደረሰባቸው መስማታቸውን ነገር ግን 22 አስከሬኖች መውጣቱን ሲማሌንጋ ተናግረዋል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተባለው የዜና ወኪል የአካባቢው የእሳትና የነፍስ አድን ተጠባባቂ አዛዥ ፋውስቲን ማቲቱ “ከእንግዲህ ወዲህ በፍርስራሹ ውስጥ የተቀበሩ አስከሬኖች ስለሌሉ” ፍለጋው ተጠናቋል ማለታቸውን ዘግቧል።

ሲማሌንጋ እንደገለጹት ቡድኑ በማዕድን በበለጸገው አካባቢ ከሦስት ሳምንታት በፊት የማዕድን ማውጣት የጀመረ ሲሆን ይህም መንግሥት የደኅንነት ሂደቶችን ከማምጣቱ በፊት ነው።

በአካባቢው እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ በማስከተሉ ምክንያት በአካባቢው ማዕድን ማውጣት ተከልክሏል።

“የክልሉ ማዕድን ሠራተኛ ጎበኝቷቸው የማዕድን ቁፋሮውን አስቆሟቸዋል” ብለዋል ሲማለንጋ።

በዓለም ትልቅ ከሆኑት የወርቅ አምራቾች አንዷ በሆነችው ታንዛኒያ ቁጥጥር ያልተደረገበት እና በሕገ-ወጥ መንገድ ማዕድን ማውጣት የተለመደ ነው።