ናይጄሪያ እና ግብፅ

ከ 2 ሰአት በፊት

በአይቮሪኮስት እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ ለዋንጫው ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል ናይጄሪያ እና ግብፅ አቻ ሲለያዩ ጋና ደግሞ ውድድሩን በሸንፈት ጀምራለች።

ናይጄሪያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ባደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 ተለያይተዋል።

ኢባን ሳልቫዶር የኢኳቶሪያል ጊኒን ጎል አስቆጥሯል።

አፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ቪክቶር ኦሲሜህ ባስቆጠራት ጎል ናይጄሪያ አቻ ለመውጣት ችላለች።

ምድቡን የውድድሩ አስተናጋጅ ሆነችው አይቮሪኮስት በመክፈቻ ጨዋታ ጊኒ ቢሳው ላይ ባስመዘገበችው ድል በሦስት ነጥብ ለመምራት በቅታለች።

ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ናይጄሪያ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዎችም ትላንት እሁድ ተከናውነዋል።

የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ግብፅ እና ሞዛምቢክን አገናኝቷል።

ፈርንኦኖቹ ጨዋታው በተጀመረ በ89ኛው ሰከንድ በሙስጠፋ ሞሐመድ ጎል ቀዳሚ ለመሆን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ዊቲ እና ስሌሲዮ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ሞዛምቢክ 2 ለ 1 ለመምራት በቅታለች።

በተጨማሪ ሰዓት ሞሐመድ ሳላህ ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ግብፅ አቻ በመለያየት ከሽንፈት ተርፋለች።

በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ምሽት ላይ ኬፕ ቬርዴ እና ጋና ተገናኝተዋል።

ጨዋታውን ኬፕ ቬርዴ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

ጃሚሮ ሞንቴሮ በ17ኛው ደቂቃ ኬፕ ቬርዴን ቀዳሚ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ጋና አቻ የሚያደርጋትን ጎል ማስቆጠር ብትችልም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮባታል።

ጋና ወደ ጨዋታው የሚመልሳትን የአቻነት ጎል በአሌክሳንደር ጅኩ አማካኝነት ማስቆጠር ችላለች።

ጨዋታው አቻ ሊጠናቀቅ ነው በተባለበት በ92ኛው ደቂቃ ጋሪ ሮድሪጌዝ ባስቆጠራት ጎል ኬፕ ቬርዴ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች።

ምድብ ሁለትንም በሦስት ነጥብ ለመምራት ችላለች።

ግብፅ እና ሞዛምቢክ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።