ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰዎችን የገቢ ልዩነት ያሰፋል
የምስሉ መግለጫ,ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰዎችን የገቢ ልዩነት ያሰፋል

ከ 5 ሰአት በፊት

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ወደፊት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) 40 በመቶ የሚሆነውን ሠራተኛ ከሥራ ውጭ ሊያደርግ ይችላል ሲል ተነበየ።

የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ከሪስታሊና ጂዮርጊዬቫ እንደሚሉት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰዎችን ሥራ መቀማቱ ሳያንስ በሰዎች መካከል ያልተመጣጠነ የገቢ ልዩነት ይፈጥራል።

ሥራ አስፈጻሚዋ ፖሊሲ አውጪዎች በዚህ ረገድ መጪውን አደጋ አይተው ተገቢውን እርምጃ መውሰድ መጀመር አለባቸው ብለዋል።

ቴክኖሎጂ ማኅበረሰብን ቀውስና አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ሊከት አይገባም ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እንደሚተነብየው ከሆነ ባደጉ አገራት ሰው ሠራሽ አስተውሎት 60% በሚሆኑ ሠራተኞች ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።

አንዳንዶቹ ሥራቸው በሰው ሠራሽ አስተውሎት ስለሚታገዝ ያተርፉ ይሆናል። ምርት እንዲጨምርም ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በሌሎች አጋጣሚዎች ግን ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ይሠሩ የነበሩ ሥራዎችን ጠቅልሎ ስለሚወስድ ሚሊዮኖችን ከሥራ ውጭ ያደረጋል።

ይህ ደግሞ መሥሪያ ቤቶች የሰው ኃይል አስፈላጊነትን እንዳይሹ ያደርጋቸዋል።

ባላደጉ አገሮች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችለው 26% ብቻ እንደሆነ ድርጅቱ ትንቢቱን አስቀምጧል።

የገንዘብ ተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ ክሪስታሊና ጂዮርጊዬቫ እንደሚሉት እነዚህ አዳጊ አገሮች ለሰው ሠራሽ ልህቀት የሚሆኑ መሠረተ ልማቶች ስለሌላቸው ወይም ስለማይኖሯቸው በሠራተኛ ኃይሉ ላይ የሚደርሰው ተጽእኖ አነስተኛ ይሆናል።

ይሁንና ይህ ሁኔታ እየቀጠለ ሲሄድ በአገሮች መካከል ያለውን የገቢ ልዩነት እያሰፋ እኩልነትን እያጠፋ ይሄዳል።

ድርጅቱ እንደሚለው ወደፊት ወጣት ሠራተኞችና ከፍተኛ ተከፋዮች ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር መራመድ ስለሚችሉ ገቢያቸው በዚያው መጠን ከፍተኛ እየሆነ ሊመጣ ይችላል።

የዓለም 14ኛውን ትልቅ አልማዝ ያገኙት ቆፋሪዎች ሕይወታቸው ምን መሰለ?ከ 6 ሰአት በፊት

በተቃራኒው በዕድሜ የገፉ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች ተፈላጊነታቸው ስለሚመናመን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ።

“አገሮች ይህን ከግምት ውስጥ አስገብተው ቴክኖሎጂው ለሚጎዳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ከወዲሁ ሴፍትኔት ሊያሰናዱ ይገባል’’ ብለዋል የተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ ጂዮርጊዬቫ ።

”ይህ ሲደረግ ነው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ መቀነስ የሚቻለው። ”

ይህ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ትንበያ የወጣው የከፍተኛ ኩባንያ መሪዎች፣ የቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚዎች እና የፖለቲካ መሪዎች ለዓለም ኢኮኖሚ ጉባኤ በስዊዘርላንድ ዴቮስ ከተማ በተሰበሰቡበት ወቅት ነው።

የቻትጂፒቲ መምጣትን ተከትሎ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በመጪው ዘመን ሊኖረው የሚችለው ተጽእኖ ከፍተኛ መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል።

ቴክኖሎጂው ምናልባት ቁጥጥር ካልተደረገበት የሰው ልጆችን ሊቆጣጠራቸው ይችላል የሚል ስጋት በስፋት ይስተጋባል።

ባለፈው ወር የአውሮፓ ኅብረት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ጊዝያዊ ስምምነት ማድረጋቸው አይዘነጋም።

የአውሮፓ ፓርላማ በበኩሉ የሰው ሠራሽ ረቂቅ ሕግ ላይ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ሕጉ ተፈጻሚነት የሚኖረው ከ2025 ዓ/ም በኋላ ይሆናል።

አሜሪካ፣ ዩኬ እና ቻይና የራሳቸው የሰው ሠራሽ ልህቀት የቁጥጥር መመሪያ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።