በጋዜጣዉ ሪፓርተር

January 14, 2024

አቶ ስንሻው ታምሩ የዓለም አቀፍ አንድነት የዕርዳታ ማዕከል ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በኢትዮጵያ ጥናታዊ ጽሑፉን ባቀረቡበት ወቅት

በናርዶስ ዮሴፍ 

የኢትዮጵያ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከ80 በመቶ በላይ የቡና ምርታቸው የተዛባ መጠን እንዲኖረው ያደረገው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮችና በተክሉ ላይ በሚከሰቱ በሽታዎች መሆኑን በጥናት መረጋገጡ ተጠቆመ። 

ዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል (International Growth Center) እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር  ‹‹ችግርን የምትቋቋም ኢትዮጵያ! በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ቀጣይነት ያለው ዕድገት!›› በሚል ርዕስ በጋራ ባዘጋጁት ዓውደ ጥናት ላይ ‹‹የአየር ንብረት ለውጥና የኢትዮጵያ ቡና›› በሚል ርዕስ የቀረበ ጥናት የችግሩን ምክንያት አመላክቷል። 

የዓለም አቀፉ ማዕከል በኢትዮጵያ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ስንሻው ታምሩ ያቀረቡት ጥናት፣ በፀሐይ ብርሃን፣ በውኃና በዝርያዎቹ ዓይነት የምርቱ ተመራጭነት አቅም ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያርፍበት የቡና ምርት፣ በሙቀት መጨመርና በበሽታዎች ምክንያት የተለያዩ መዛባቶች እያጋጠሙት እንደሆነ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ የአየር ንብረት እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ በየአሥር ዓመቱ ቢያንስ የ0.25 ዲግሪ ሲልሺየስ ሙቀት ዕድገት ጭማሪ እያስመዘገበ ሲሆን፣ በዓመት ውስጥ ከፍተኛ ሙቀት የሚመዘግብባቸው ቀናት ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱም ተብራርቷል። 

የቡና ምርት አርሶ አደሮችን በመጠየቅ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ‹‹አንድ ጥሩ የምርት ዓመት ካሳለፍን ቀጣዩ መጥፎ ይሆንብናል ያሉት 40 በመቶ፣ አንድ ጥሩ የምርት ዓመት አሳልፈን ተከታታይ ሁለት መጥፎ ዓመታትን እናስተናግዳለን ያሉት 38 በመቶ›› ናቸው። ከአጠቃላይ አርሶ አደሮች 16 በመቶው እያጋጠመን ያለውን የምርታማነት መዛባት በዓመታት መድቦ ማስቀመጥ ይቸግረናል ማለታቸውም ተጠቅሷል።

ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2015 ዓ.ም. ባለው አሥር ዓመታት ውስጥ ከቡና ተክል በሽታዎች ጋር በተያያዘ ትልቅም ይሁን ትንንሽ በሽታዎች በምርቱ ላይ ያጋጠማቸው አርሶአደሮች ብዛት ከነበረበት 70 በመቶ ወደ 86 በመቶ ከፍ ብሏል። የቡና ተክል በሽታዎች አላጋጠመንም ያሉ አርሶአደሮች መጠንም ከ19 ወደ 26 በመቶ ከፍ ማለቱም ተነግሯል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ስንሻው ‹‹የአየር ንብረት ለውጥ አንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን ለቡና ምርት የበለጠ ተስማሚ እያደረገ ሲመጣ፣ ሌሎችን ደግሞ ተስማሚነታቸውን እያሳጣቸው ነው፤›› ብለዋል።

በጥናቱ በአሁን ወቅት የዓረቢካ ቡና ዓይነት በአገሪቱ ካለው ሽፋን በ2050 ዓ.ም.  የአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚነት በማጣት ምክንያት  በግማሽ ያህል ሊቀንስ ይችላል የተባለ ሲሆን፣ የቡና ተክል ዘርን ለማባዛት የሚያግዙ የንብ መንጋ መቀነስም አንዱ ችግር ነው በሚል ቀርቧል። 

ከአየር ንብረት ተስማሚነት ጋር ሊከሰት የሚችልን የምርት ማጣት ለማስቆም፣ የአርሶ አደሮች በሌላ አካባቢዎች መስፈርና የቡና ተክሎችንም ከፍታ ባላቸው ሥፍራዎች ላይ ማስፋፋት እንደ መፍትሔ ቢጠቀሱም፣ ለእነዚህ ግን ከፍተኛ ዝግጅትና ፈንድ ይጠይቃል ተብሏል። 

የቡና ምርታማነቱን ለማሳደግ በዓለም አቀፉ ማዕከል ጥናት የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ የዕድገት አማራጭ መንገዶችና ዕቅዶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። 

በረጅም ጊዜ ዕቅዶች ሥር የጥላ ዛፎችን መትከል፣ የተለያዩ የቡና ተክል ዓይነቶችን ማሠራጨትና ማልማት፣ እንዲሁም የቡና ተክል ልማት አካባቢዎችን መቀየር ተካተው ቀርበዋል። 

በአጭር ጊዜ ዕቅዶች ሥር ገለባና የበሰበሱ ቅጠሎችን እንደ ማዳበሪያ መጠቀም (Mulching)፣ የቡና ዛፎችን መከርከም (Pruning)፣ እና እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ (Value Adding) ተጠቅሰዋል። 

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ስንሻው ‹‹አርሶ አደሮች የሚያጋጥማቸውን የቡና ተክል በሽታ መከላከል እንዲያስችላቸው የፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን እንዲጠቀሙ ብንመክርም ተግባራዊነቱ ግን ዜሮ በሚባል ደረጃ ነው፤›› ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለ ሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ቡናችን ተፈጥሯዊ በመሆኑ ነው የሚታወቀው። በዓለም አቀፍ ገበያ የተፈጥሯዊ ቡና ሽያጭ ዋጋ ከፍ ስለሚል፣ ለተፈጥሯዊነቱ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይሰጣል። ፀረ ተባይ ኬሚካል ከተጠቀሙ ይህ አይሆንም፣ ስለዚህ ፀረ ተባይ አንጠቀምም፣ አርሶ አደሮቻችንም እንዲጠቀሙ አንመክርም፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ከዓለም አምስተኛዋ የቡና ምርት አቅራቢ አገር ስትሆን፣ ከአገሪቱ ጥቅል አገራዊ ምርት ዕድገት 35 በመቶ ድረስ በቡና ምርት በሚገኝ ገቢ እንደሚሸፈን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃዎች ያሳያሉ። 

የዓለም አቀፉ ማዕከል ጥናት ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርስ ብዛት ያላቸው ሰዎች፣ ወይም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ16 እስከ  20 በመቶ የሚሆነው በቡና ምርት እርሻ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች መሆናቸውን ያሳያል።