የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ለግዳጅ ብቁ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ

ዜና የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ለግዳጅ ብቁ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ
ቀን: January 14, 2024
በአዋጅ እንደገና ከተቋቋመ ስድስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል፣ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጾ፣ ለግዳጅ ብቁ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1947 ዓ.ም. የተቋቋመውና በደርግ ዘመን ሦስት ሺሕ አባላት እንደነበሩት የሚነገርለት የቀድሞው የባህር ኃይል፣ ኤርትራ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር አጥታ ወደብ አልባ ስትሆን ሙሉ በሙሉ መፍረሱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ጠቅላይ የሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ባህር ኃይልን እንደገና በአዋጅ ማደራጀት መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ ባህር ኃይሉ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከዝግጅት ባለፈ ግዳጆችን ሲወጣ መቆየቱን፣ አሁን ደግሞ ግዳጅ ለመወጣት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የባህር ኃይል ምክትል አዛዥ ሪር አድሚራል ናስር አባዲጋ አስታውቀዋል፡፡
ምክትል አዛዡ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት በአካል በመገኘት የተቋሙን እንቅስቃሴ በገመገምበት ወቅት ነው፡፡ ሪር አድሚራል ናስር በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ጥሩ ቁመና የነበረው የታጠቀ ባህር ኃይል የነበራት ቢሆንም፣ እንዲፈርስ በመደረጉ፣ እንደ አዲስ በማደራጀት አሁን ለውጊያ የሚሆን አቅም ተገንብቷል ብለዋል፡፡
በአገር ውስጥና በተለያዩ አገሮች ለአራትና ለስድስት ወራት ተገቢውን ሥልጠና ወስደው መርከብ ይዘው ባህር ላይ የቆዩ አባላት፣ በብቁ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ለሚያጋጥሙ ግዳጆች ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችውን ተናግረዋል፡፡
ከአገሮች ጋር በትብብር መሥራትን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ከሶማሌላንድ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ብልፅግና ከሚፈልጉ አካላት ሁሉ በጋራ እንደሚሠራ፣ በአገር ውስጥ ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ከሐዋሳና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት መደረጉን ምክትል አዛዡ አስረድተዋል፡፡
አክለውም ሲጠናቅቅ 240 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል ያሉትን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሱዳን በ50 ደቂቃ ውስጥ የጉዞ ርቀት ውስጥ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ‹‹አካባቢውን በብቃት መጠበቅና ግዳጅ መፈጸም የምንችልበት ደረጃ ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡
የወጭና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴው ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ፣ ባህር ኃይሉ አገሪቱ ባሏት ሐይቆች ጭምር ጥበቃ የማድረግ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ አገሮች ቢደመሩ ሕዝባቸው ከ130 ሚሊዮን በላይ እንደማይሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት 120 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር በጣም ትንሽ ልዩነት ያለው ነው ያሉት ምክትል አዛዡ፣ ከአገሮቹ ጋር በጋራ በመስማማት መሠራት አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ጂቡቲ ጁባ ሳይቀር ጫትና መሰል ሸቀጦች ከእኛው አገር ነው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ ሳይጎዳዱ በጋራ መኖር የሚቻልበት መንገድ ፈጥሮ መኖር እንጂ፣ አይ እኔ ልኑር አንተ አትኑር የሚል አስተሳሰብ መቆም አለበት፤›› ብለው፣ ‹‹ኢትዮጵያውያንም ብንሆን ነገር ከማቀሳሳር ስለኢትዮጵያ ዕድገት ማሰብ ስላለብን ሰይጣንዊ ሥራ መቆም አለበት፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መሃዲ (ዶ/ር) ለሚዲያ ዝግ የነበረውን የባህር ኃይል አጠቃላይ ሪፖርት ተከትሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማበራሪያ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ባህር ስለሌላት የባህር ኃይል አያስፈልጋትም›› የሚል ሳይንስ የለም ብለዋል፡፡ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙ በአዋጅ እንደገና ከተቋቋመ በኋላ ጠንካራ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ መሠረታዊ ሸቀጦች ማንም ሊጠብቅ ስለማይችል፣ በገነባችው የባህር ኃይል ይጠበቃል፣ በመሆኑም ይህንን ወጪና ገቢ ሀብት መጠበቅና ህልውናውን የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል፡፡ በተጨማሪም ቀጣናው ካለበት የደኅንነት ሥጋት አንፃር የሚታዩትን ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር፣ የባህር ላይ ወንበዴዎች፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ለመጠበቅ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፤›› ብለዋል፡፡ በአገር ውስጥና በዓለም አሉ ከሚባሉ ታዋቂ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በመሆን በሠራው ሥራ ባህር ኃይሉ ጠንካራ ቁመና ላይ ይገኛል በማለት አስታውቀዋል፡፡