አበበ ፍቅር

January 14, 2024

በኢንተር ፕራይዝ ለተደራጁ በአማራ ክልል ወጣቶች በ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ይሰጣል ከተባለው 3.3 ቢሊዮን ብር መደበኛና ተዘዋዋሪ የገንዘብ ፈንድ ብድር፣ 547 ሚሊዮን ብር ብቻ ወይም 16.5 በመቶ ብቻ ያህሉ መቅረቡን የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ።

ከተሰጠው የብድር አገልግሎት ውስጥ 367.5 ሚሊዮን ብር ከፀደይ ባንክ በመደበኛ ፈንድ መገኘቱን፣ 181 ሚሊዮን ብር ደግሞ 2009 ዓ.ም. የዓለም ባንክ በአገር ደረጃ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከሰጠው አሥር ቢሊዮን ብር ለክልሉ ከደረሰው 2.6 ቢሊዮን ብር ተቀንሶ መሆኑን፣ የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

 በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ለሚሠሩ ወጣቶች በዋሊያ ካፒታልና በልማት ባንክ አማካይነት ለተለያዩ ማሽነሪዎች መግዣ ከታቀደው 700 ሚሊዮን ብር፣ 50 ሚሊዮን ብር ብቻ መገኘቱን ምክትል የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

የ2016 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት አፈጻጸምን ቢሮው ከወዲሁ ገምግሞ ሪፖርት ማቅረቡን የተናገሩት አቶ አወቀ፣ ከ2014 እና 2015 ዓ.ም. ከነበረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ሲወዳደር በእጅጉ መቀነሱን አስረድተዋል።

ለዚህ ምክንያቱ በክልሉ ያለው አለመረጋጋት እንደሆነ የተናገሩት አቶ አወቀ፣  የኢንተርኔት መዘጋትም ሌላኛው ተግዳሮት ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ክልሉ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ያህል ወጣቶችን በሥራ አጥነት ለመመዝገብ ማቀዱን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ እስካሁን 594 ሺሕ ወጣቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

ከተመዘገቡት ወጣቶች የሥራ ፈጠራና የሥራ አመራር፣ እንዲሁም የቴክኒክ ሥልጠና ወስደው 486  ሺሕ ብቻ ብቁ ሆነው መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

ይህ አኃዝ ከ2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቅናሽ መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን፣ 1.2 ሚሊዮን ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊው የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው እንደነበር ምክትል የቢሮ ኃላፊው አስታውሰዋል።

 አክለውም 261 የመሥሪያ ሼዶችን ለተደራጁ ወጣቶች መስጠታቸውን ገልጸው፣ 25,500 ሔክታር መሬት ለማስተላለፍ ታቅዶ 2,500 ሔክታር መሰጠቱን አብራርተዋል።

በክልሉ ካለው የፀጥታ ችግር ከፍተኛውን የወጣቶች ቁጥር ይይዛሉ ተብሎ የሚታሰቡት ምሥራቅ፣ ምዕራብና ሰሜን ጎጃም ምዝገባ አለማድረጋቸውን አቶ አወቀ ተናግረዋል።

በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ቢሆን ባለው አለመረጋጋት ሁሉም ሥራ ፈላጊ ወጣቶች እንዳልተመዘገቡ የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ በሥራ ላይ ያሉት ወጣቶች በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እየሆኑ ነው ለማለት ያስቸግራል ብለዋል።

ወጣቶችን ባሉበት አካባቢ በበይነ መረብ ለመመዝገብ የሚያስችል ሲስተም  ተዘርግቶ የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት በመዘጋቱ ሲስተሙን ሳይጠቀሙ መቅረታቸውን አክለዋል።