ደብሊው ኤችኤች የተሰኘው ድርጅት የአምስት ዓመቱን ፕሬግራም ይፋ ባደረገበት ወቅት

ማኅበራዊ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ቢያድግም ለአካባቢያዊ ድርጅቶች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ቢያድግም ለአካባቢያዊ ድርጅቶች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: January 14, 2024

በኢትዮጵያ የተመዘገቡ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ከ4,700 በላይ ቢደርስም፣ በአካባቢያዊ መዋቅር የሚገኙትና በርካታ ቁጥር ያላቸው ድርጅቶች የሚሰጣቸው ትኩረት አነስተኛ መሆን አሳሳቢ ነው ተባለ፡፡

በጀርመን መንግሥት የሚደገፈውና ደብሊውኤችኤች (WHH) የተሰኘው ድርጅት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በታችኛው አካባቢያዊ መዋቅር ለሚገኙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በአምስት ዓመታት የሚተገበር የ402 ሚሊዮን ብር ፕሮግራም ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

ይፋ በተደረገው በዚህ ፕሮግራም ላይ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁመናና እያጋጠማቸው ያሉ ማነቆዎችን በተመለከተ፣ የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡

አቶ ደበበ በዳሰሳ ጥናታዊ ጹሑፋቸው በአገር ውስጥ እየተመሠረቱ ያሉት የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ቢጨምርም፣ ከውጭ ከሚመጣው ድጋፍ ማነስና ካላቸው የአቅም ውስንነት ጋር ተደምሮ ለኅብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ ደርጅቶች ትኩረት እንደማይሰጣቸውና ይህም ካልተስተካከለ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ድርጅቶቹ ለኅብረተሰቡ ቅርብ ቢሆኑም፣ በቅርበታቸው ልክ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዳይወጡ እንደገደባቸው አስረድተዋል፡፡

በርካታ የሚባሉ አነስተኛ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ወደ አንድ ሊያመጣና በጋራ በማሰባሰብ እንዲሠሩ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ሌላኛው ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፀጥታ ችግር ምክንያት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት አለመቻል፣ ተሻሽሎ የነበረው የሲቪክ ምኅዳሩ አንደገና እየጠበበ መምጣት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፖሊሲ አወጣጥ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ውስን መሆን፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና ቦታ ማጣት የሲቪክ ድርጅቶች ሚናቸውን እንዳይወጡ ማነቆ እንዳደረገባቸው አቶ ደበበ አስረድተዋል፡፡

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ረቂቅ ፖሊሲ ከተዘጋጀ የቆየ ቢሆንም እስካሁን ባለመፅደቁ፣ ድርጅቶች በረጅም ጊዜ ዕቅዶች ከመሳተፍ ይልቅ በአጫጭር ፕሮጀክቶች እንዲወሰኑ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡

ደብሊውኤችኤች የተሰኘው ድርጅት ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እስከ እ.ኤ.አ. 2028 የሚቆየው ፕሮግራም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚፈጸም ነው፡፡ በዋነኝነት አካባቢያዊ ለሆኑ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት፣ እንዲሁም በሥልጠና አቅም በመፍጠርና በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚታየውን ጥሩ ያልሆነ አመለካከት የማስተካከል ሥራ ይከናወናል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉት አጠቃላይ የሲቪክ ማኀበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት አካባቢያዊ መሠረት እንዳላቸው፣ ቀሪዎቹ 30 በመቶ የሚሆኑት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡