የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት የ2015/16 ሪፖርት በቀረበበት ወቅት

ማኅበራዊ በትራፊክ አደጋ ከሚሞቱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ተባለ

አበበ ፍቅር

ቀን: January 14, 2024

በየዓመቱ በትራፊክ አደጋ ከሚሞቱት የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ አምራች የሆኑት ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የ2015 ዓ.ም. የትራፊክ አደጋ መረጃ ትንተና ውጤቶችን ይፋ አድርጓል፡፡

በቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው በ2015 ዓ.ም. 408 ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው አኃዝ 40 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የሞት አደጋ ከደረሰባቸው 86 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች ሲሆኑ፣ ይህ አኃዝ ላለፉት ተከታታይ ስድስት ዓመታት የቀጠለ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተነግሯል፡፡

አደጋዎቹ በብዛት የሚከሰቱት ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት እስከ 2፡00 ሰዓት እንደሆነ የታየ ሲሆን 50 በመቶ የሚሆነው አደጋ የደረሰው ደግሞ ዓርብን ጨምሮ በቅዳሜና እሑድ ቀናት መሆኑ በጥናት ተደርሶበታል ተብሏል፡፡

በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከፍተኛውን የሞት መጠን እንዳደረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ12 እስከ 16 ተሳፋሪዎችን የሚጭኑ ሚኒባሶች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ እንደነበር በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

የአደጋዎቹ ዋና ዋና መንስዔዎችና አደጋውን ለመቀነስ በቀጣይ ምን መሠራት አለበት በሚሉት ሐሳቦች ዙሪያ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

በየወቅቱ የሚወጡ ሕጎች በአግባቡ አለመተግበር ለችግሩ መስፋፋት በር ከፋች ነው ሲሉ አሥር አለቃ አብነት ምትኩ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ተናግረዋል፡፤

አንዳንድ የትራፊክ መብራቶችና የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች ጉብታዎች (ብሬከሮች) አላስፈላጊ በሆኑና በደንብ ባልተጠኑ መንገዶች ላይ ሲተከሉ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንደሚያመዝን አስተያየት ሰጭው ገልጸዋል፡፡

የአደጋዎቹ መንስዔዎች በደንብ አልተጠኑም ያሉት አሥር አለቃ አብነት፣ ተሽከርካሪዎች እንዲያልፉ የሚያዘው መብራት ሲበራ አሽከርካሪው የእግረኞችን እንቅስቃሴ በትኩረት ሊመለከት ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም ከሰሞኑ አንዲት የአካል ጉዳተኛ ሴት መንገድ በማቋረጥ ላይ እያለች በደረሰባት አደጋ ሕይወቷ ማለፉን አስተያየት ሰጭው ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ ከተጠቀሱት ችግሮች በላይ እንዴት መሻሻል እንዳለባቸው ጥናቱ ቢያመለክት፣ የተሻለ ነበር ያሉት የሚኒባስ ታክሲ ማኅበር አባል አቶ አያሌው ሥዩም ናቸው፡፡

አቶ አያሌው እንዳሉት ከዚህ የተሻለ ሥራ የሚሠራው አሽከርካሪዎችን በመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ለአሽከርካሪዎች ስለአደጋው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሥልጠና በመስጠት ነው፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ ወጭ ወጥቶባቸው የተሠሩ የመንገድ ዳር ምልክቶችና ሌሎች ንብረቶች እንደቀልድ ሲባክኑ እየተመለከቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለይ የተለዩ ክፍለ ከተሞች ላይ ከትራፊክ ማኔጅመንት ጋር በመሆን የሚሠሩት ሥራዎች ዝቅተኛ ናቸው ሲሉ አስተያየት ሰጭ ተናግረዋል፡፡

የፍጥነት መቀነሻ ጉብታዎች በተለይ ምሽት ላይ በጣም አስቸጋሪና ለሌላ አደጋ የሚያጋልጡ ናቸው ያሉት አስተያየት ሰጭው፣ ብዙዎቹ አካባቢዎች የምሽት መብራት ባለመኖሩ ተጨማሪ አደጋ እያደረሱ ነው ብለዋል፡፡