
January 15, 2024 – EthiopianReporter.com
ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ በኩል የባህር በር የሚያስገኝላትን የመግባቢያ ሰነድ ታኅሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተፈራረመች በኋላ፣ ሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛቴ ተጣሰ በማለት ጩኸት ማሰማት በመጀመሯ በአፍሪካ ቀንድ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚሉ መላምቶች እየተሰሙ ነው፡፡ የመግባቢያ ስምምነቱን ተከትሎ ውዝግብና ቀጣናዊ ሥጋት የተፈጠረ ቢሆንም፣ ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር የሚያገናኛት የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ለብዙ ጊዜያት ሲወተወት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለቀይ ባህርም ሆነ ለኤደን ባህረ ሰላጤ በቅርብ ርቀት ላይ ሆና ወደብ አልባ መሆኗ ለመግባቢያ ስምምነቱ መፈረም ምክንያት ሲሆን፣ ምንም እንኳ የስምምነቱ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም ሶማሌላንድ የኢትዮጵያን ዕውቅና በልዋጩ እንደምታገኝ መሰማቱ ለውዝግብ መነሻ ሊሆን ችሏል፡፡ ሶማሌላንድ እ.ኤ.አ. በ1991 ከዋናዋ ሶማሊያ ተለይታ ነፃነቷን ብታውጅም፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና ሳይሰጣት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ለንግድም ሆነ ለመከላከያ የሚሆን የባህር በር በአካባቢው ማግኘት የሚገባት ቢሆንም፣ በሶማሊያ በኩል የተሰማው ተቃውሞ የቅርብና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶችን እያስተባበረ ስለሆነ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ማሳሰቢያውንና ሥጋቱን ሲገልጽ ሰንብቷል፡፡ እንደ አውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ አሜሪካ፣ ወዘተ ሦስቱ አገሮች ውጥረት አስወግደው ንግግር እንዲጀምሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ግብፅና የዓረብ ሊግ ከሶማሊያ ጎን መቆማቸውን በግልጽ አስታውቀዋል፡፡ ሌሎች ያደፈጡ አገሮችና ትብብሮችም አሉ፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት ለዓባይ ወንዝ ውኃና ለአካባቢው ሥጋት መሆኑን በማስታወቅ፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ከተገኘች በአካባቢው የሚኖራትን ተፅዕኖ እንደሚያሳጣት ነው ፍራቻዋ፡፡ በዚህም ምክንያት የሶማሊያን ሉዓላዊ ነፃነት የሚጋፋ ስምምነት ነው በማለት የራሷን ጥቅም ለማስከበር ስትል ጠላትነቷን አሳይታለች፡፡ ግብፅ በዋናነት አባል የሆነችበት የዓረብ ሊግም ልክ እንደ ግብፅ የሶማሊያ የግዛት አንድነት መከበር አለበት ነው ያለው፡፡ የዓረብ ሊግ ለሶማሊያ በግልጽ ነው የትግል አጋርነቱን የገለጸው፡፡ ጎረቤት ኤርትራና ግብፅ ሽር ጉድ የጀመሩ ሲሆን፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አስመራ ደርሰው መመለሳቸው የራሱ መልዕክት አለው፡፡ ሌሎችም ጥቅማቸውን እያሰሉ አቋማቸውን እንደሚያሳዩ ይጠበቃሉ፡፡
ሶማሊያ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ያሰማችው ተቃውሞ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት አግኝቶ ነው የሰነበተው፡፡ የብዙዎቹ ሥጋት ወትሮም ነውጥ ተለይቶት የማያውቀው የአፍሪካ ቀንድ ወደ ለየለት ትርምስ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ሲሆን፣ የጂኦ ፖለቲካው ውጥረት ሲባባስም በአካባቢውና በሩቅ ያሉ ዓለም አቀፍ ተዋንያንን እንደሚስብ ይገምታሉ፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ምንም እንኳ የመግባቢያ ሰነዱ ስምምነት ዝርዝር ባይታወቅም ኢትዮጵያ፣ ሶማሌላንድና ሶማሊያ ውጥረቱን በማርገብ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ለማገዝ የሚሹ እንዳሉም ይሰማል፡፡ በእርግጥም ሁሉንም ወገኖች ሊያግባባ የሚችል ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት ምን መደረግ አለበት የሚለው ሊያሳስብ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል መደረግ አለበት ተብሎ የሚታሰበው በተቻለ መጠን ለመልካም ጉርብትናና ወዳጅነት ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በብልኃት፣ በጥበብ፣ በብስለትና በስክነት የሚመራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል፡፡ ዲፕሎማሲውን በስክነት ለመምራት የሚያግዙ በርካታ ባለሙያዎች ስላሉ፣ አላስፈላጊ ውዝግቦችን ወደ ጎን በማለት አዋጭ ተግባራት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡
አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ አገሮች ከኢትዮጵያ በስተቀር በቅኝ የተገዙ በመሆናቸው፣ የቅኝ ግዛት ትሩፋት የሆኑ ሁከቶችና ግጭቶች ከበፊት ጀምሮ በስፋት ተንሰራፍተዋል፡፡ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡት ሁሉም አገሮች ከመተባበር ይልቅ አንዱ የሌላውን ተቃዋሚ በመደገፍ ያባከኑት የሰው ኃይል፣ ጊዜና ሀብት ከድህነት ውስጥ መንጥቆ ያወጣቸው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚፈሱ ወንዞች ሌሎች አገሮችን በሚገባ ከማልማት አልፈው፣ የሚገኙ ምርቶች ለጋራ ዕድገት መዋል ይችሉ ነበር፡፡ ሁሉም አገሮች ያሏቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎች ተረዳድተው ለማልማት ቢያውሉ ኖሮ የአፍሪካ ቀንድ የግጭት፣ የድርቅና የረሃብ መጫወቻ አይሆንም ነበር፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች መንግሥታት እርስ በርስ መስማማት አቅቷቸው አንዱ የሌላውን ሚሊሻ ከማሠልጠን ይልቅ፣ ተባብረው አገሮቻቸውን ለማልማት የጋራ ፍኖተ ካርታ ቢያዘጋጁ ኖሮ ዜጎቻቸው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ በመሆን ምፅዋት ጠባቂ አይሆኑም ነበር፡፡ ለዚህ ስላልታደሉ ግን አንደኛው መሪ ከሌላው መሪ ጋር ጠብ ውስጥ ሲገባ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› እያሉ የጥፋት ሩጫ ይጀምራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከእንዲህ ዓይነቱ አስከፊ የፖለቲካ ጥልፍልፎሽ ውስጥ መውጣት የምትችለው፣ መንግሥት ራሱ ሰከን ብሎ በዕውቀትና በጥናት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ነው፡፡ ለባህር በር ፍለጋውም ሆነ ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራት የሚያስፈልገው በባለሙያዎች የተመከረበት የሰከነ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር የሚያስፈልጋት ብሔራዊ ጥቅሟንና ደኅንነቷን ለማስጠበቅ እንጂ፣ የማንኛውም አገር ወይም ስብስብ ቃፊር ለመሆን እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አካባቢውን ወደ አውዳሚ ጦርነት ሊያስገባ የሚችለው የሩቅም ሆኑ የቅርብ ኃይሎች ተቀፅላ መሆን ሲጀመር ነው፡፡ መንግሥት አሁንም ከሁሉም ጎረቤት አገሮች ጋር በወዳጅነትና በትብብር በጋራ አብሮ መኖርና መሥራት እንደሚፈልግ፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ ለሚገኙ ኃይሎች ሳይቀር በግልጽ ማስታወቅ አለበት፡፡ እግረ መንገዱንም በባህር በር ፍለጋ ጥረት ውስጥ በራሱ በኩል የፈጠራቸው መደነቃቀፎች ካሉም ማረም ይጠበቅበታል፡፡ ዋናው ቁምነገር የባህር በር አስፈላጊነት ትንተና ሳይሆን፣ ፍለጋው ሕጋዊና ፍትሐዊ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚሰጡ ማብራሪያዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ይሁኑ፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ግንኙነታቸው በአመዛኙ በደም አፋሳሽ ጦርነት የተሸፈነ ነው፡፡ ለዚህም በቂ ምክንያቶች አሉ፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ቻርተር መሠረት ሁሉም አገሮች በቅኝ ግዛት ዘመን በተሰመሩ ድንበሮች እንዲፀኑ ቢደነገግም፣ ሶማሊያ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ማግሥት ጀምሮ ‹‹በታላቋ ሶማሊያ›› ቅዠት ከኢትዮጵያ ጋር በግዛት ይገባኛል ጥያቄ በተደጋጋሚ ተዋግታለች፡፡ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከጂቡቲና ከኬንያም ይገቡኛል የምትላቸው ግዛቶች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በተደጋጋሚ ባደረገቻቸው ጦርነቶች ተሸንፋም ሆነ ከዚያ በኋላ በደረሰባት መፈራረስ ውስጥ ሆና፣ አንድ ችግር ባጋጠመ ቁጥር በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ለጠብ መጋበዝ ልማዷ ነው፡፡ ይህንን የቆየ ልማድ በአካባቢው ያሉ አገሮችን ብቻ ሳይሆን በሩቅ ያሉትን ጭምር በተለያዩ ተዛምዶዎች በኢትዮጵያ ላይ ለማስነሳት ትጠቀምበታለች፡፡ የሰሞኑ የግብፅና የዓረብ ሊግ መወራጨት የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጡንነት የሚጎድለው እንቅስቃሴ መገደብ የሚቻለው አብሮ በመጯጯህ አይደለም፡፡ ይልቁንም የአፍሪካ ኅብረትን፣ ኢጋድን፣ ተመድንና ሌሎች አጋሮችን በማስተባበር ወደ ንግግርና ድርድር በማምራት ነው፡፡ የወቅቱ ሁኔታም በሰከነ ዲፕሎማሲ ይመራ!