
January 15, 2024 – EthiopianReporter.com
የተስፋፋው የወንጀል ድርጊት እስከ መቼ?
በአዲስ አበባ ለከተማ በተለያዩ ቦታዎች የስርቆትና የዝርፊያ ወንጀሎች ተበራክቷል፡፡ ወንጀሎች ሲፈጸሙም ዓይን ባወጣ መልኩና በጠራራ ፀሐይ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡
በተደራጁ ጭምር የሚደረጉ ዝርፊዎች ዕለት በዕለት እየጨመሩ ሲሆን፣ የእጅ ስልክ፣ ቦርሳ፣ ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ ሌሎች ዝርፊዎችም እየተፈጸሙ መሆኑን፣ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜ ከሚያሰሙት ቅሬታና ከከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ዘገባዎች መረዳት ይቻላል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነቱ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የስርቆትና የወንጀል ድርጊት ሊስፋፋ መቻሉን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የወንጀል ድርጊቱም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ እየተፈጸመ ነው፡፡
ከተማዋ ከአንድ ወር በፊት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው በቡድን የተደራጁ ሞባይሉንና ገንዘቡን ከዘረፉት መካከል ወጣት ሀብታሙ ዓባይ ይገኝበታል፡፡ ወጣቱም ከኢምፔሪያል ወደ ሳሪስ አቦ በሚወስደው መንገድ ትራንስፖርት በመጠባበቅ ላይ እያለ ነው፡፡ ትራንስፖርት የሚሰጡ አስመስለው ዘረፋ ያከናወኑበት፡፡በወቅቱም ድርጊቱ የተፈጸመበት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ እንደሆነ የሚያስረዳው ይህ ወጣት፣ ዘረፋውም ሲፈጸምበት በመኪና ውስጥ ሁለት ሴቶችና አራት ወንዶች እንደነበሩ ይናገራል፡፡ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመበት ዋነኛ ምክንያት ኢምፔሪያል አካባቢ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች በርካታ ቢሆኑም፣ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሰዎች ግን አለመኖራቸውንና ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ እነዚህ ተሽከርካሪ ገብቶ ትራንስፖርት ሲጠቀም ሊዘረፍ መቻሉን ያብራራል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱን ሲጠቀም ብዙም ጥርጣሬ እንዳላደረበት የገለጸው ወጣቱ፣ ከኢምፔሪያል ተነስቶ ልክ ካርጎ አካባቢ ሲደርስ ገንዘብና ሞባይሉን ወስደውበት ከመኪናው አውጥተው እንደወረወሩት ያስረዳል፡፡ ድርጊቱም ሲፈጸም ለተወሰነ ሰዓት ድንጋጤ አድሮበት እንደነበርና በሰውነቱ ላይ በትንሹም ቢሆን ጉዳት እንደደረሰበት ያስታውሳል፡፡
ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ የሆነውን ነገር ለፖሊሶች ማስረዳቱን ጠቅሶ፣ ፖሊሶቹም እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች በከተማዋ በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ መሆኑንና ለቀጣይም ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንደመከሩት ለሪፖርተር ይገልጻል፡፡
የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመ በሦስተኛው ቀን ፖሊስ ጉዳዩን ምን ላይ እንዳደረሰው ለመጠየቅ ሲሄድ ተገቢውን ምላሽ አለማግኘቱንና ከማመልከት ውጪ ሌላ ጥቅም አለማግኘቱ ንዴት ውስጥ እንደከተተው ይናገራል፡፡
ከዚህ በፊት ሁለት ጓደኞቹ በተለያዩ ጊዜያት ባለሦስት እግር ባጃጅ ውስጥ ስልካቸው እንደተሰረቀና በከተማዋም እንዲህ ዓይነት ድርጊት በተለያዩ ጊዜያት እንደሰማ ጠቁሟል፡፡ በእርግጥ የወንጀል ድርጊት በከተማዋ ሊስፋፋ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ነው የሚለው ይህ ወጣት ችግሩንም መንግሥት በአፋጣኝ መፍታት ካልቻለ በየጊዜው የወንጀል ድርጊቱ እየተስፋፋ ይመጣል ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ከሥራ ወጥቶ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመግባት ላይ እያለ ሞባይሉን የተዘረፈው አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት ለሪፖተር እንደገለጸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው የተለያዩ ዘረፋዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ አዲስ ሠፈር ወደ ተከራየበት የመኖሪያ ቤት በመሄድ ላይ እያለ ሁለት ሰዎች ከኋላ ከኋላ እየተከተሉት እንደነበርና ነገሩንም ችላ በማለቱ ዘረፋው ሊፈጸምበት እንደቻለ ያስረዳል፡፡
በወቅቱም ድርጊቱ ሲፈጸምበት የተከራየበት መኖሪያ ቤት ገባ ያለና ለዝርፊያ አመቺ እንደሆነ የሚገልጸው ወጣቱ፣ ዘረፋው ሲፈጽሙበት አንዱ ከኋላ ሲያንቀው ሌላው ደግም ኪሱ ውስጥ ያለውን ሞባይልን ሊወስደው መቻሉን ያብራራል፡፡
አዲስ ሠፈር ለዘረፋ የሚያመች አካባቢ እንደሆነ ገልጾ፣ አካባቢው ላይም ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለሦስት ሆነው ሊዘርፉት መሞከራቸውንና የአካባቢው ሰው እንዳዳነው ይገልጻል፡፡
ከዚህ በፊት ፍቅረኛውን እዚያው አካባቢ ገና በ12፡00 ሰዓት ላይ ቦርሳዋንና ስልኳን እንደሰረቋት የሚያስታውሰው ይህ ወጣት፣ አካባቢውም የተለያዩ ፀጉረ ልውጥ ሰዎች ስለሚበዙበት ሌባውን ከጤነኛው ለመለየት ከባድ ነው ይላል፡፡
በተለይ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ሲዘረፉ እንደሚሰማና በአካባቢው ፖሊስ ጭምር ወደ ውስጥ መግባት እንደሚፈራ ገልጾ፣ በርካታ የአካባቢው ማኅበረሰብ አንድነት ሠፈሩን እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዘረፋና የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ቢመጡም የፖሊስ አካል ጉዳዩን ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠው ያስረዳል፡፡
ከሁሉም በላይ በተለያዩ ቦታዎች በቡድን ተደራጅተው የሚዘርፉ መብዛታቸውን፣ በአንድ ወቅትም መገናኛ አካባቢ በመኪና እየተዘዋወሩ ሲዘርፉ የተገኙ ወንጀለኞች ተይዘው ማየቱን ይገልጻል፡፡
የወንጀል ድርጊቱን ለመከላከል ማኅበረሰቡ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት የሚለው ይህ ወጣት፣ ይህ ካልሆነ አብዛኛዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ችግር ውስጥ ይወድቃሉ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ጓደኛዋ ጋር አምሽታ ወደ መኖሪያ ቤቷ እያቀናች የተዘረፈችው ወ/ሮ ማኅሌት ታከለ፣ ሳሪስ አካባቢ ከምትኖረው ጓደኛዋ ቤት አምሽታ ወደ መኖሪያ ቤቷ በመሄድ ላይ እያለች ነበር ዘረፋ የተፈጸመባት፡፡
በወቅቱም ወንጀሉ የተፈጸመው ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ እንደሆነ፣ ምሽት ላይም በአካባቢው ላይ የታክሲ አገልግሎት ስለማይኖር የሞላ ላዳ አግኝታ በመሄድ ላይ እያለች የመኖሪያ ቤቷ የመዳረሻ አካባቢ ቦርሳዋንና ሞባይሏን ቀምተው እንደገፈተሯትና በሰውነቷ ላይ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባት ታስረዳለች፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱንም ስትጠቀም በላዳ ታክሲ ውስጥ ሰው ስለነበር ዘረፋው ይደርስብኛል ብላ እንዳላሰበችና በኋላ ላይ ከእሷ ጋር የነበሩት የተደራጁ ሌቦች መሆናቸው መረዳቷን ትገልጻለች፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በቡድን ተደራጅተው የሚዘርፉ ግለሰቦች መብዛታቸው በየጊዜው እየተነገረ ነው፡፡
በተለይም መኪና፣ ሞባይል፣ የቤት ዕቃዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በመዝረፍ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሰማሩ ቡድኖች መብዛታቸውን፣ ከዚህ በፊትም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ‹‹ሃምሳ ስምንት ሠፈር›› ከዝቅ ብሎ በሚገኝ ፀበል በሚባል ሠፈር ተከራይተው የሚኖሩ ቀማኞች ከ200 በላይ ስልክ ሰርቀው መያዛቸውን ሪፖርተር ለመመልከት ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለአንድ ወር ባካሄዱት ኦፕሬሽን በዝርፊያና በሌሎች ወንጀሎች የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ወር በሦስተኛ ሳምንት ባከናወኑት ኦፕሬሽን በርካታ ተጠርጣሪዎች የያዙ ሲሆን፣ 778 መዝገቦችን አደራጅተናል ሲል በመግለጫቸው አሥፍረዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሞቱማ ሲና እንደገለጹት፣ ድንገተኛ በተደረገ ፍተሻ የተለያዩ ሰነዶች አመሳስለው ሲያትሙ የነበሩ ተገኝተው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
በተለያዩ ቤቶች በተደረገው ፍተሻም በቁጥር 502 የመሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ማኅተም፣ 26 ጥቅል ዕፅ፣ 85 ሺሻ፣ እንዲሁም 925 የቁማር ማጫወቻ ቁሳቁሶች ተይዘዋል፡፡
ከውንብድና ወንጀል ጋር በተያያዘ ሾፌሮችን በመግደል የተዘረፉ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ተከታትሎ በመያዝ ለባለቤቶቹ መመለስ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል 10 ሽጉጦች፣ 39 ታብሌትና ኮምፒዩተሮች፣ 1,835 የመኪና ዕቃዎች፣ 994 ሞባይሎችና 45 ቴሌቪዥኖች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መያዛቸውም ተገልጿል፡፡