

ወርክሾፑ በተከናወንበት ወቅት
ማኅበራዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጥራታቸው ተጠብቆ ባለመገንባታቸው ዕድለኞች ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን አንድ ጥናት…
ቀን: January 14, 2024
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ጥራታቸው ተጠብቆ ባለመገንባታቸው፣ በዕጣ የቤት ባለቤት የሆኑ ዕድለኞች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን፣ የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረት (ACRC) እና ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› (FSS) በጋራ ባደረጉት ጥናት ማረጋገጥ መቻላቸውን አስታወቁ፡፡
ሁለቱ ተቋማት ለአንድ ዓመት ያህል ባደረጉት ጥናት ከስድስት በላይ ከፍተኛ ተመራማሪዎች የተሳተፉ መሆናቸውንና ጥናቱም በኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊ ሽግግርና በወጣቶች አቅም ግንባታና በመኖሪያ ቤቶች ላይ መደረጉን ሐሙስ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የጥናቱ ውጤት ይፋ ሲደረግ ተገልጿል፡፡
የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረት ተመራማሪና የምርምር ሥርፀት አስተባባሪ ኢዛና ዓምደወርቅ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከመነሻውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም፡፡
መንግሥት 40/60 ወይም የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በዕጣ ለደረሳቸው ሲያቀርብ ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ ስለማይገነቡ፣ ዕድለኞች መልሰው አፍርሶ ለመሥራት እንደሚገደዱና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ ገልጸዋል፡፡
የእነዚህ የሦስት ጥናቶች ግኝት በቃለ መጠይቅና በዶክመንት ዳሰሳ ታግዞ የቀረበ ሲሆን፣ የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረት አዲስ አበባን ጨምሮ በአሥራ ሁለት የአፍሪካ ከተሞች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥናት ማድረጉን አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ለሥራ ተስማሚ የሆኑ ነገሮች እንደሌላቸው በጥናቱ ላይ መታየቱን ገልጸው፣ ወጣቶችም በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ፣ በኢመደበኛ ዘርፍና በጤና ላይ ያላቸውን በጎ ተግባራትና ያሉባቸው ችግሮች ተለይተው በጥናቱ ሊካተት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
‹‹በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት አብዛኛውን ነገሮች ከፍተኛ ችግር ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል፤›› ያሉት አስተባባሪው፣ ያሉትንም ችግሮች በጥናቱ በመለየትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ትርጉም ያለው ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡፡
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አብዛኛውን የቤት አቅርቦት ተፈጻሚ የሚሆነው በመንግሥት እንደሆነ፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ቤት አልሚ ድርጅቶች ተቋቁመው የማኅበረሰቡን የቤት ጥያቄ እየመለሱ መሆናቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን በቤት አቅርቦት ላይ ለውጦች እየመጡ ቢሆንም አሁንም የመሬት አቅርቦት፣ እንዲሁም በዝቅተኛና በመካከለኛ ገቢ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቤት ለመሥራት ቢፈልጉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው ዕድለኞች ለኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ፣ የሲራሚክ ንጣፍ፣ ለመፀዳጃ ቤት መስመር፣ ግድግዳ እንደገና ለመሥራትና ሌሎች የጎደሉ ነገሮች ለማሟላት ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳረጉ ጥናቱ ያሳያል፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ መንግሥት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከግብዓት ጀምሮ እስከ ባለሙያ ድረስ ጥራታቸውን በመጠበቅ ማቅረብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ጥናት የተደረገባቸው እነዚህ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትና በጥናቱ የቀረቡ ግኝቶች መሬት ወርደው ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች የሚቀርቡ መሆናቸውን አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት በክረምት በጎ ፈቃድ የሚታደሱ ቤቶችን በተቋም ደረጃ ሥርዓት ተበጅቶ መከናወን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን እንቅስቃሴ ዕውን የሚያደርጉ ዘርፎችን በመለየት ጥናት መደረጉን፣ የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረት ተመራማሪ ተገኝ ገብረ እግዚአብሔር (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሠረት በትራንስፖርት፣ በውኃ፣ በደረቅ ቆሻሻ፣ በጤና ዘርፍና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ ‹‹ምን ዓይነት ችግሮች አሉባቸው? ምን ዓይነት መልካም ጎኖች አሏቸው?›› የሚለውን መለየት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ይህንን መሠረት አድርጎ በተጠናው ጥናት እያንዳንዱ ዘርፍ ከፖሊሲ ችግርና ከሕግ አንፃር የተዳሰሰ መሆኑን፣ በተለያዩ ዘርፎች አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡
በተመሳሳይ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃቸው በጣም ውስን እንደሆነ ገልጸው፣ የእነዚህንም ኢንተርፕራይዞችን መሠረታዊ ችግሮቻቸውን መፍታት ካልተቻለ ካሉበት ዘርፍ ወደ ቀጣይ ለመሸጋገር ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ኢዛና (ዶ/ር) አክለው ገልጸዋል፡፡
