

ማኅበራዊ ለስምንት ክልሎች ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተጀመረው ፕሮጀክት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ
ቀን: January 14, 2024
- ለፕሮጀክቱ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል
በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች በተመረጡ አሥር ወረዳዎች፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃና ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተጀመረው ፕሮጄክት አፈጻጸሙ ከ20 በመቶ በታች መሆኑ ተጠቆመ፡፡
‹‹ወተር ፎር ላይፍ ፕላስ›› የተሰኘው ፕሮጀክት በስምንት ክልሎች፣ በአሥር ወረዳዎች የመጠጥ ውኃና ከፀሐይ ለሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ፕሮጀክት ቢቀርፅም፣ የታቀደለትን ያህል መጓዝ አለመቻሉን፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት ገልጿል፡፡
ዓርብ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና የመብራት አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ እንዲሁም ለአካባቢ ነዋሪዎች አገልግሎቶቹን ተደራሽ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ‹‹Child Inevestment Fund Action (CIFF)›› የተባለ በጎ አድራጎ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ፕሮጀክት ቀረፆ መግባቱ ተጠቅሷል፡፡
ፕሮጀክቱ ከጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ የካቲት 21 ቀን 2019 ዓ.ም. ለአምስት ዓመታት ተቀርፆ ወደ ሥራ ቢገባም፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለ800,000 የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ቢታቀድም፣ በአንፃሩ የተከናወነው ለ224,359 የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆኑ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
ይህም ታቅዶ ከነበረውና 28.04 በመቶ ብቻ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ሊቆፈሩ ከታቀዱት 244 ጉድጓዶች የተከናወኑት 45 ብቻ በመሆናቸው፣ 18.44 በመቶ ብቻ መሳካቱ ተገልጿል፡፡
ለ‹‹ወተር ፎር ላይ ፕላስ›› ፕሮጀክት የተመደው በጀት 79,888,350 ዶላር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 64,378,523 ዶላር ማለትም 80.59 በመቶ ቀጥታ የፕሮጀክቱን ወጪዎች እን
ደሚሸፍን በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
ለፕሮጀክቱ ከተመደበው በጀት መካከል 15,509,826.01 ዶላር ወይም 19.41 በመቶ የሚሆነው ለአስተዳደራዊ ወጪዎች እንዲውል መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
‹‹ከቺልድረን ኢንቨስትመንት ፈንደ ፋውንዴሽን›› (CIFF) ከተባለ ተቋም ጋር በትብብር የተጀመረውን ፕሮጀክት ‹‹ወርልድ ቪዥን›› (World Vision) የፕሮጀክቱን ሥራ ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ደካማ አፈጻጸም ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዝርዝር የሥራ ሒደቱን በተመለከተ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራውን ከሚሠራው ወርልድ ቪዥን ሪፖርት የቀረበለት ሁለት ጊዜ ብቻ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
በኦዲት ግኝቱ መሠረት በወተር ፎር ላይፍ ፕላስ (Water for Life Plus) ፕሮጀክት የቧንቧ ቱቦ ጥራቱ በብሔራዊ ደረጃ በተቀመጠው መመርያ መሠረት በውኃ ጉድጓድ ውስጥ አለመገጠሙ ተገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት የተቆፈሩት የውኃ ጉድጓዶች የረዥም ጊዜ አገልግሎት ዘመን እንዳይሰጡ ከማድረጉም በላይ በተዘረጉ የውኃ መውጫ ቱቦዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ተነስቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር 17 የውኃ ጉድጓዶች የፍሎራይድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የሌላቸው መሆኑን በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
በአንፃሩ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ባቀረበው ሪፖርት የአራት ውኃ ጉድጓዶች ላይ ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን መኖሩን እንጂ፣ በእያንዳንዱ የውኃ ጉድጓድ ላይ ምን ያህል ፍሎራይድ መጠን እንዳለ አለመገለጹ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል የተቆፈረው ጉድጓድ ከተጠናው ወይም ከታቀደው ጋር ሲነፃፀር ልዩነት ማሳየቱ በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል፡፡
ይህም ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ አጠቃላይ በሁለት ዓመታት የሚቆፈረው ጉድጓድ መጠን 97 ቢሆንም የተሠራው ግን 86 እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱን እንዲያጠና ኃላፊነት የወሰደው ስትሪንግ ኮሚቴ ሪፖርት መሠረት፣ አጠቃላይ የሚቆፈረው የውኃ ጉድጓድ መጠን ቁጥር 83 መሆኑን፣ በአንፃሩ የተሠራው ግን 70 እንደሆነ በመግለጹ የሪፖርቱን ትክክለኛነት በአግባቡ መረጋገጥ እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በዕቅዱ ተይዞ ከተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ምንም ዓይነት ውኃ ያላመነጩ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ የተገለጸ ቢሆንም፣ በተደረገው ማጣራት 11 ጉድጓዶች ደረቅ መሆናቸው መረጋገጡን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል፣ የንብረት፣ የፋይናንስ ብክነት ማስከተሉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ የንፁህ መጠጥ ውኃ እንዳያገኝ ዳርጎታል ተብሏል፡፡
ሌላው በፕሮጀክቱ ተካትቶ የነበረው ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማቅረብ ሒደት ሲሆን፣ ይህም የሶላር ፓኔል ዝርጋታና የኮንትሮል ቦክስ ተከላው ደረጃውን ጠብቆ ያልተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የወርልድ ቪዥን የቆጠራ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ ለውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ግንባታ የሚያገለግሉ ንብረቶች ብዛት 1,402 ተገዝተው ገቢ ከተደረጉት ውስጥ በከፊል ሥራ ላይ ውለው፣ በስቶር የሚገኙ 7,034፣ በድምሩ 8,436 የሚሆኑ ንብረቶች ጥቅም ላይ ሳይውሉ በመጋዘን መቀመጣቸው ተገልጿል፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርት ባቀረበበት መድረክ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተወካዮች ጥሪ እንደቀረበላቸው ቢጠቀስም በዕለቱ አለመገኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
