
ከ 2 ሰአት በፊት
በኦሮምያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ከአንዲት የ24 ዓመት ወጣት ሴት ጭንቅላት ውስጥ ጥይት በቀዶ ሕክምና መውጣቱ ተገለጸ።
በወለጋ ዩኒቨርስቲ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል ሁለት ሰዓት የፈጀውን ቀዶ ሕክምና የመሩት ዶ/ር ዋቅቶሌ አብዲሳ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ወጣቷ ለስድስት ቀናት በሆስፒታሉ ካገገመች በኋላ የጤና መሻሻል አሳይታ ወደ ቤቷ መሄዷን ተናግረዋል።
በምዕራብ ወለጋ የመነ ሲቡ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው የ24 ዓመት ሴት ወደ ሆስፒታሉ ከመምጣቷ በፊት በወረዳው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ለስድስት ቀናት ያክል ቀላል የሕክምና ድጋፍ ሲደረግላት መቆየቱን ዶ/ር ዋቅቶሌ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“እኛ ጋር ስትመጣ ራሷን አታውቅም ነበር። . . . የደረሰባት ጉዳት ለሕይወቷ አስጊ ነበር። በጥይት የተመታው የአንጎሏ ክፍል ከጥቅም ውጪ መሆን ጀምሮ ነበር” ይላሉ።
የሆስፒታሉ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ሃኪም ጥይቱ ለስድስት ቀናት በጭንቅላት ውስጥ ቆይቶ ስለነበረ የታካሚዋ የራስ ቅሏ ሲከፈት የአንጎሏ ክፍል የመበስበስ ምልክት ማሳየቱን እና መጥፎ ጠረን ፈጥሮ እንደነበረ ጨምረው ገልጸዋል።
ይህች ወጣት እንዴት በጥይት ልትመታ እንደቻለች፣ አሁን ስላለችበት የጤና ሁኔታ እንዲሁም በጥይት መመታቷን ተከትሎ የተከፈተ የወንጀል ምርመራ ካለ በሚል ታካሚዋን እና ወላጆችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ወላጆች የደኅንነት ስጋት አለን በማለታቸው ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።
- ሰሞነኛው የአፍሪካ ቀንድ ትኩሳት፡ ከኢጋድ እና የአረብ ሊግ ስብሰባ እስከ የካይሮ ጉብኝት15 ጥር 2024
- በመርሐቤቴ ወረዳ ከትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገደሉ15 ጥር 2024
- የቀድሞው የዩናይትድ፣ ቼልሲ እና ማድሪድ አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ከሮማ ተባረሩከ 4 ሰአት በፊት
ዶ/ር ዋቅቶሌ ከዚህ ቀደም እንደዚህ ያለ ውስብስብ የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና በወለጋ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ተከናውኖ ስለማያውቅ ታካሚውን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ተሞክሮ እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለመላክ ከቤተሰቧ ጋር ተነጋግረን ነበር” የሚሉ ዶ/ር ወቅቶሌ፤ ቤተሰብ ግን ወጣቷን አዲስ አበባ ወስደው የሚያሳክሙበት፤ ሕይወቷ ቢያልፍ እንኳ አስክሬን ይዘው ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው ለተጨማሪ ሕክምና ታካሚዋን ወደ አዲስ አበባ ወስዶ በማሳከሙ ሃሳብ ሳይስማሙ መቅረታቸውን ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎም የሆስፒታሉ ሐኪሞች ቀዶ ሕክምናውን በሆስፒታሉ ለማድረግ ከወሰኑ በኋላ ዝግጅት ማድረግ መጀመራቸውን ሃኪሙ ያስረዳሉ።
“የሲቲ ስካን ምርመራ ጥይቱ የፊተኛው የጭንቅላቷ ክፍል እንዳለ ያሳያል። የራስ ቅል ተሰብሮ አእምሮ የሚሸፍነውን ‘ዱራ’ እንደቀደደ ያሳያል” በማለት ሁኔታውን ይገልጻሉ።
በወቅቱ ራሷን ስታ የነበረች ታካሚ ታኅሣሥ 27/2016 ዓ.ም. በስድስት የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ሁለት ሰዓት የፈጀ የተሳካ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።
“የጭንቅላቷን የፊተኛ ክፍል ከፍተን ጥይቱን አወጣን። ተሰብሮ ወደ አእምሮ ውስጥ የገባውን የራስ ቅል ስባሪ አውጥተን፤ ተቀዶ የነበረውን አእምሮን የሚሸፍነውን ‘ዱራ’ መልሰን ሰፋን” በማለት የተደረገውን ሕክምና ሃኪሙ ይገልጻሉ።
ዶ/ር ዋቅቶሌ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ለአንድ ሳምንት ያክል ለታማሚዋ በሆስፒታሉ የቅርብ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
“በየዕለቱ መሻሻሎችን ታሳይ ነበር። ባለፈው አርብ ደግሞ (ጥር 3/2016 ዓ.ም.) ሙሉ በሙሉ መሻሻል አሳይታ ወደ ቤቷ ሄዳለች” ብለዋል።
ሃኪሙ ከዚህ ቀደም መሰል ውስብሰብ ቀዶ ሕክምና ተከናውኖ በማይታወቅበት ሆስፒታል የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና መደረጉ የጤና ባለሙያዎችን በራስ መተማመን እንደሚጨምር ገልጸዋል።
“የዚህን ሕዝብ መቀነት ፈትተን ነው በሕዝብ ገንዘብ የተማርነው። በእውቀታችን እና በፈጣሪ እርዳታ ታግዘን ይህን ሕዝብ ለማገልገል እንሰራለን” ብለዋል።