ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አላደረሰም
የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አላደረሰም

ከ 9 ሰአት በፊት

በየመን የሑቲ አማጺያን በአሜሪካ መርከብ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ሰነዘሩ። ጥቃቱን ያደረሱት ‘ጂብራልተር ኤግል’ በተሰኘው አቃ ጫኝ ግዙፍ መርከብ ላይ ነው።

የመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ማዘዣ ማዕከል ጥቃቱ በየመን ጠረፍ አካባቢ መፈጸሙን አምኖ ነገር ግን የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ አብራርቷል።

የማርሻል አይላንድ አርማን የያዘው ይህ መርከብ ጉዞውን በኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጥሏል።

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሑቲዎች በቀይ ባሕር አካባቢ የባሕር ጉዞን ማስተጓጎል የጀመሩት እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት በመቃወም ነው።

‘ኤግል በልክ’ የተሰኘው የመርከብ ድርጅት እንዳለው መርከብ ብረት ጭኖ ከኤደን ጠረፍ 160 ኪሜ ምትር ርቀት ላይ እየተጓዘ ነው ጥቃቱ የደረሰበት።

ጥቃቱ ያደረሰው ጉዳት መጠነኛ ስለነበረ መርከቡ ጉዞውን ቀጥሏል ብሏል ኩባንያው።

አሜሪካ እንዳለችው ከዚህ የሚሳኤል ጥቃት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ሌላ ሚሳኤል በሑቲዎች የተተኮሰ ቢሆንም በአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች አየር ላይ እንዲመክን ሆኗል።

ይህ ሚሳኤል ዒላማ አድርጎ የነበረው በቀይ ባሕር የአሜሪካ ባሕር ኃይልን ነበር።

ሑቲዎች የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን እንደሚቀጥሉ ዝተዋል።

ሆኖም ጥቃቶቹ በሁሉም የንግድ መርከቦች ሳይሆን ከእስራኤል ጥቅም ጋር የተሳሰሩ ላይ ብቻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ሑቲዎች ጥቃቶቹ የሚቀጥሉት እስራኤል በጋዛ በሐማስና በንጹሐን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት እስከቀጠለች ድረስ ነው።

የዩኬ ባሕር ኃይል ይህ ጂብራልተር ኤግል መርከብ ከእስራኤል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጫለሁ ብሏል።

ሑቲዎች በሰጡት ምላሽ ደግሞ የአሜሪካ ማንኛውም ጥቅም ላይ ጥቃት እንሰነዝራለን ብለዋል።

ናሲር አል ዲን የተባሉ የሑቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ‘’የአሜሪካ የሆነ መርከብ ሁሉ ጥቃት ሊሰነዘርበት ይገባል’’ ብለዋል።

በቀይ ባሕር ሑቲዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ በርካታ ግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች ጉዟቸውን በሌላ አቅጣጫ ለማድረግ ተገደዋል። ይህ ደግሞ በዓለም የንግድ መርከብ ሰንሰለት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው።

የትናንቱን የሑቲዎች ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር የአሜሪካ ባንዲራ ያላቸው እና የአሜሪካ ንብረት የሆኑ መርከቦች በቀይ ባሕር የተወሰኑ አካባቢዎች እንዳይጠጉ መክሯል።

ሰኞ ዕለት በዓለም ሁለተኛው ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያ የሆነው ኳታር-ኢነርጂ መርከቦች በቀይ ባሕር በኩል እንዳያልፉ ውሳኔ አስተላልፏል።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካና ዩኬ በሑቲ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ከባድ ጥቃት መሰንዘራቸው አይዘነጋም። ጥቃቶቹ የሑቲዎችን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሽመደምደው ይጠበቃል።

ጥቃቶቹ በአየርና ከባሕር የተነሱና በአሜሪካ አጋሮች የጋራ ጥምረት የተሰነዘሩ ሲሆን የሑቲ ሚሳኤሎች እና የአየር መቃወሚያዎች የሚገኙበትን የየመን የጦር ሰፈር ዒላማ ያደረገ ነበር።

ጥቃቱን ተከትሎ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ 13 የሑቲ የአየር ጥቃት መነሻ ነበሩ የተባሉ የጦር ሥፍራዎች እንዳልነበሩ ሆነው ወድመዋል ብለዋል።

የአሜሪካ ደኅንነት በበኩሉ ከአጋሮች ጋር ባለፈው ሳምንት የመን ላይ የተሰነዘረው ጥቃት አንድ ሦስተኛውን የሑቲዎች የጦር መሣሪያን አውድሟል።

ዋሺንግተን ኢራንን ከሑቲ የሚሳኤል ጥቃት ጀርባ አለች ስትል ትከሳለች፤ ኢራን ታስተባብላለች።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሑሴን አሚር አብዱላሒ ትናንት ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምዕራባዊያን በየመን ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት ማቆም አለባቸው ብለዋል።