January 16, 2024 

የብልፅግና አገዛዝ በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶችን አፍኖ በግፍ እያሰረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

የጥምቀት እና ከተራ በዓልን የሥልጣኑ ስጋት አድርጎ የቆጠረው የኦሕዴድ /ብልፅግና አገዛዝ እንደ ከዚህ ቀደሙ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እያፈነ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

ሕዝባዊ በዓላትን የሥርዓቱ ጠላት እና አደጋ እንደሆኑ አድርጎ የሚቆጥረው አገዛዙ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችን በማፈንና በማሰር ለቤተክርስቲያኒቱም ሆነ ለሀገሪቱ ድምቀት የሆነው የጥምቀት በዓል እንዳይከበር እየሰራ መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ወጣቶቹ ከቤታቸው፣ ከመንገድ ላይና በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ በአገዛዙ ኃይሎች እየታፈኑ ታስረዋል። በአዲስ አበባ የሚገኙ እስር ቤቶች በወጣቶች መሞላታቸውንና እስሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ጭምር መሆኑም ታውቋል።

እስሩ በቅርቡ ከዚህ ቀደም በነበሩት የአደባባይ በዓላትን አስታኮ ይደረግ የነበረ ቢሆንም፤ ያሁኑ እስር ግን በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን በሰጠችው መግለጫ ተደናግጦ እንደሆነ መረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን “መንግሥት” በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ያልተገባ ጫና እዲያቆም ማሳሰቧ እና ይህ ካልሆነ ግን የራሷን መፍትሄ እንደምትወስድ መግለጿ ይታወሳል።

ከትናንት ሰኞ ጀምሮ የአገዛዙ ኃይሎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከሥራ የሚመለሱ የከተማዋን ነዋሪዎች ከመኪና እያስወረዱ ሲፈትሹ ማምሸታቸውም ታውቋል።

አገዛዙ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በምዕመናን ላይ መዋቅራዊ እና ስልታዊ የሆነ ጥቃት በዕቅድ እየፈፀመ መሆኑ ይታወቃል። ይህንንም እኩይ ድርጊቱን እንዲያቆም ባልደራስ በተደጋጋሚ መግለጫዎች በመስጠት ሲያሳስብ ቆይቷል።

አሁንም ባልደራስ እንዲህ አይነቱን በቤተክርስቲያኒቱ እና በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የሚያደርገውን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆም ያሳስባል።

የግፍ እስረኞች ይፈቱ!
ድል ለዲሞክራሲ! ምንጭ ባልደራስ ፓርቲ