ካሪም ቤንዜማ

ከ 4 ሰአት በፊት

ፈረንሳዊው እግር ኳስ ኮከብ ካሪም ቤንዜማ ስሙን ከሙስሊም ወንድማማቾች (ሙስሊም ብራዘርሁድ) ጋር ያያዙትን የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ላይ የስም ማጥፋት ክስ መስርቶባቸዋል ሲሉ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ዤራልድ ዳርማኒን ጥቅምት ላይ እንደገለጹት ቤንዜማ ከሱኒ ሙስሊም እስላማዊ ቡድን ጋር “የሚታወቅ ግንኙነት” አለው።

ይህ ክብሩን እና ስሙን “ያጎድፋል” ሲሉ የቤንዜማ ጠበቃ ተናግረዋል።

የሙስሊም ብራዘርሁድ ግብጽ፣ ሩሲያ እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ታግዷል።

ባለፈው ጥቅምት ተጫዋቹ “ሴቶችን እና ህጻናትን የማይለይ ኢፍትሃዊ የቦምብ ጥቃት ሰለባዎች” ሲል ድጋፉን ለጋዛ ነዋሪዎች በኤክስ ከገለጸ በኋላ ነው ዳርማኒን አስተያየታቸውን የሰጡት።

መስከረም 26 በሐማስ ለተገደሉት አንድ ሺህ 300 እስራኤላውያን ተመሳሳይ ሃዘኔታ አለማሳየቱን የገለጹት ዳርማኒን፤ ፈረንሳዊው አጥቂ “ከሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር ግንኙነት እንዳለው ቀድሞውን የታወቀ ነው” ብለዋል።

“የጂሃድ ድባብ ስለሚፈጥር የሙስሊም ብራዘርሁድ የሆነውን ጭራቅ እየተዋጋነው ነው” ሲሉ ፖለቲከኛው ለወግ አጥባቂው የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲ ኒውስ ገልጸዋል።

የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነውን እና በሳዑዲ አረቢያ የሚጫወተው የ36 ዓመቱ ካሪም ቤንዜማ ውንጀላውን ውድቅ አድርጎ በሚኒስትሩ ላይ የስም ማጥፋት ክስ እንደሚመሰርት አስጠንቅቆ ነበር።

የሙስሊም ብራዘርሁድ የተመሰረተው የዛሬ 80 ዓመት ገደማ ግብጽ ውስጥ ነበር። ሐማስን ጨምሮ ለብዙ ዘመናዊ እስላማዊ ድርጅቶች መመስርት ምክንያት ሆኗል።

በዋነኛነት ምንም ዓይነት መደበኛ መዋቅር የሌለው የርዕዮተ ዓለም እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። በበርካታ አገሮች ውስጥ የተከለከለ ቢሆንም በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ ህብረት አገራት ውስጥ አልታገደም።

ዤራልድ ዳርማኒን

በፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን በሰፊው በተዘገበው ባለ 92 ገጽ ክስ “ከሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር ግንኑነት ኖሮኝ አያውቅም፤ እስከማውቀው ድረስ የድርጅቱ አባል ከሆነ ሰው ጋርም ግንኙነት የለኝም” ብሏል።

ጠበቃው ሁጉስ ቪጊየር ለፈረንሳዩ ጋዜጣ እንደተናገሩት እግር ኳስ ተጫዋቹ “የፖለቲካ መጠቀሚያ” እንደሆነ እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን “በፈረንሳይ መከፋፈልን እየዘራ ነው” ሲልም ከሷል።

ዳርማኒን ቀደም ሲልም ካሪም ቤንዜማን ዒላማ አድርገው ነበር። የፈረንሳይን ብሄራዊ መዝሙር ለመዘመር ፈቃደኛ ባለመሆኑ እና “በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ሃይማኖትን መስበክን” ጨምሮ በሌሎች ምክንያቶች ከሰውታል።