የእስራኤል 'ዓይኖች'

ከ 6 ሰአት በፊት

የእስራኤል ‘ዐይኖች’ በመባል ይታወቃሉ። ሁሉም ወጣት ሴቶች ናቸው። መቀመጫቸው ጋዛ ደንበር ላይ ነው።

ወጣቶቹ ድንበሩ ላይ አንድ ሥራ ብቻ ነው ያላቸው። ድንበር ላይ በመሆን ለሰዓታት ቅኝት በመድረግ ማንኛውንም አጠራጣሪ እንቅስቀሴ መከታተል ነው ብቻኛው ኃላፊነታቸው።

እነዚህ ወጣት ሴቶች ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ድንገት ከፈጸመው ጥቃት በፊት አጠራጣሪ ነገሮችን ድንበር አካባቢ ማየት ጀመሩ።

የወረራ እና የእገታ አፈጻጸም ልምምድን ይመለከቱ ነበር። ፍልስጤማውያን ገበሬዎችም እንግዳ የሆነ ባህሪ ሲያሳዩ ነበር።

ኖአ [ስሟ ተቀይሯል] የሚያዩትን መረጃ ለስለላ እና ከፍተኛ መኮንኖች ያስተላልፉ እንደነበር ትናገራለች። የተሰጣቸው ኃላፊነትም ይህ ብቻ ነበር። ሌላ ምንም አቅም አልነበራቸውም። “እኛ ዐይኖች ብቻ ነበርን” ትላለች።

ለአንዳንዶቹ ሐማስ አንድ ትልቅ ነገር እንዳቀደ ግልጽ ነበር። ለኖአ ሁኔታው “ሊፈነዳ የተቃረበ ፊኛ” ዓይነት ነበር።

ቢቢሲ እነዚህን ወጣት ሴቶች አነጋግሯቸዋል። ስላዩት አጠራጣሪ እንቅስቃሴ፣ ስላቀረቧቸው ሪፖርቶች እና የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ምላሽ አለመስጠታቸው ላይ አተኩሯል።

ሴቶቹ ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በፊት በነበሩት ወራት በድንበር ላይ ስለተከሰቱ ጉዳዮችም በዋትስአፕ የተለዋወጧቸው መልዕክቶችን ተመልክቷል። የማይቀረው ጥቃት ሲመጣ “ማን ተረኛ ይሆናል?” የሚለውንም አንዳንዶች ጠይቀው ነበር።

የማንቂያ ደውሉን ያሰሙት እነዚህ ወጣት ሴቶች ብቻ አልነበሩም።

ከጥቃቱ በኋላ ግን የአገሪቱ ጦር ጥቃቱን ቀድሞ እንዴት ማስቆም እንዳልቻለ ለሚቀርብለት ጥያቄ “ትኩረቴ የአሸባሪው ድርጅት ሐማስን ስጋት በማስወገድ ላይ ነው” በሚል ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።

በአንድ የድንበር ጥብቃ ቡድን ውስጥ አባል የነበረችው የቀድሞዋ አዛዥ ለቢቢሲ እንደተናገረችው “ዋናው ችግር እነሱ [ጦሩ] የቀረቡለትን ሃሳቦች አቀናጅቶ አለመረዳቱ ነው።”

ጦሩ የቀረቡለትን የተበጣጠሱ መረጃዎችን ቢያጤን ኖሮ ሐማስ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ለተባለለት ጥቃት እያደረገ የነበረውን ዝግጅት ቀድሞ ይረዳ ነበር ትላለች።

መስከረም 26 ድንበር ላይ ዐይናቸውን ተክለው ጥበቃ ላይ ከነበሩት መካከል የ19 ዓመቷ ሻይ አሽራም አንዷ ነበረች። ከቤተሰቦቿ ጋር ባደረገችው የመጨረሻ የስልክ ጥሪ ከጀርባዋ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር። “አሸባሪዎች አሉ። ትልቅ ችግር ሊፈጠር ነው” ስትል ተናግራ ነበር።

ሻይ አሽራም
የምስሉ መግለጫ,በመስከረም 26ቱ ጥቃት በሐማስ የተገደለችው ሻይ አሽራም

በዕለቱ ከተገደሉት በርካታ የእስራኤል የቅኝት ወታደሮች መካከል አንዷ ነበረች። ሌሎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።

ሐማስ ጥቃት መስንዘር ጀመረ። ከጋዛ ድንበር አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ናሃል ኦዝ በሚገኘው የመቆጣጠሪያ ጣቢያ የነበሩ ሴቶች በሚጋሩት የዋትስአፕ ግሩፕ እርስ በእርስ መሰነባበት ጀመሩ።

ኖአ በዕለቱ ሥራ ላይ አልነበረችም። መልዕክቶቹን እያነበበች “በቃ ይኸው ነው” ማለቷን ታስታውሳለች። ለረዥም ጊዜ ሲፈሩት የነበረው ጥቃት አሁን እየደረሰ ነው።

የእነዚህ ሴቶች ወታደራዊ ክፍል ታትዝፒታኒዮት በመባል ይታወቃል። በጣቢያቸው አቀማመጥ ምክንያት ሐማስ ወረራ ከፈጸመባቸው የመጀመሪያዎቹ እስራኤላውያን መካከል ሆነዋል።

“ሥራችን ሁሉንም ነዋሪዎች መጠበቅ ነው”

ሴቶቹ በድንበር አቅራቢያ በሚገኙት ክፍሎች ውስጥ ለሰዓታት ይቀመጣሉ። ትኩረታቸው ደግሞ ከቅኝት ካሜራዎች የተገኙ ምስሎችን በቀጥታ መከታተል ነው። ድንበር ላይ በሚገኙት አጥሮች ላይ ከተተከሉት ካሜራዎች እና በጋዛ ሰማይ ላይ ከሚያንዣብቡት የቅኝት ፊኛዎች ጋር ምስሎቹን ያገኛሉ።

ተመሳሳይ ኃላፊነት ያላቸው በርካታ ቡድኖች አሉ። ብዙዎቹም ጋዛ ድንበር አቅራቢያ ይገኛሉ። ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ እስራኤል ድንበሮች ላይ ተሰማርተዋል። ሁሉም የቡድኑ አባላት ሴቶች ናቸው። ዕድሜያቸው በአስራዎቹ መጨረሻ እና በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ናቸው። ጠመንጃ አይታጠቁም።

ሴቶቹ ትርፍ ጊዜያቸውን ዳንስ በመለማመድ፣ ምግብ በማብሰል እና የቲቪ ፕሮግራሞችን በመከታተል አብረው ያሳልፋሉ። ለብዙዎች ውትድርናም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው መኖር የመጀመሪያቸው ነው። በዚህም የእህትማማችነት ትስስር እንደፈጠሩ ይገልጻሉ።

ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር እንደሚወጡ ግን ይናገራሉ። “ሥራችን ሁሉንም ነዋሪዎች መጠበቅ ነው። በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው ያለን። በፈረቃ እንሠራለን። መንቀሳቀስም ሆነ ለሰከንዶች እንኳን ዐይናችንን እንድናነሳ አይፈቀድልንም። ሁልጊዜም ትኩረት መስጠት አለብን” ስትል ኖአ ስለሥራቸዋ ትናገራለች።

“ስለ ጠላት ሁሉንም ነገር የሚያውቁት” የእስራኤል ታላላቅ የስለላ ክፍሎች እና የታትዝፒታኒዮት አባላት መሆናቸውን የአገሪቱ ጦር መስከረም መገባደጃ ላይ ባሳተመው ጸሑፍ አመልክቷል።

ሴቶቹ አጠራጣሪ ነገር ሲያዩ ለበላይ አዛዦቻቸው ያሳውቃሉ። በኮምፒውተር ላይ በመመዝገብም በባለሥልጣናት እንዲገመገሙ ያደርጋሉ።

የሐማስ የስልጠና ቪዲዮ

በጡረታ የተገለሉት ሜጀር ጄነራል ኢታን ዳንጎት እንደሚሉት ታትዝፒታኒዮት “አስጊ ነገር መኖሩን በማሳወቅ ትልቁን ሚና ይጫወታሉ።”

ተቆጣጣሪዎቹ ሴቶች ማንኛውንም ስጋት የሚያሳየውን “የእንቆቅልሹን ቁልፍ” ይሰጣሉ ብለዋል።

ሐማስ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሐማስ የፈጠረው ስጋት በቁጥጥር ስር መዋሉን የሚገልጹ መግለጫዎችን ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ ነበር።

ይሁን እንጂ ድንበር ላይ ስጋት መኖሩን የሚጠቁሙ በርካታ ምልክቶች ግን ነበሩ።

መስከረም ማብቂያ ላይ የናሃል ኦዝ ተቆጣጣሪ በሚጋሩት ዋትስአፕ ላይ “ይገርማል፣ ሌላም ክስተት አለ?” በማለት ጽፋለች።

“ውዴ የት ነበርሽ? ላለፉት ሁለት ሳምንታት በየቀኑ እንመለከት ነበር” የሚል የድምጽ ምላሽ በፍጥነት ተሰጣት።

ከመስከረም መጨረሻው ጥቃት በፊት ባሉት ወራት የታዘቧቸው ክስተቶች ጥቃት እየመጣ ነው ብለው እንዲጨነቁ እንዳደረጋቸው ቢቢሲ ያነገጋራቸው አንዳንድ ሴቶች ገልጸዋል።

አሁንም በወታደርነት እያገለገለች የምትገኘው ኖአ “ወረራው ምን እንደሚመስል በሚያሳይ መልኩ በየቀኑ ሲለማመዱ እናያቸዋለን። ታንክ እንዴት እንደሚማርኩ የሚለማመዱበት ሞዴል ታንክ ነበራቸው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የሐማስ የስልጠና ቪዲዮ

“በድንበሩ አጥር ላይ የጦር መሳሪያ ሞዴል ነበራቸው። እንዴት እንደሚያፈነዱት ይለማመዱ ነበር። አጥሩን እንዴት እንደሚያጠቁ፣ እንደሚዘርፉ እና እንደሚገድሉ ይለማመዱ ነበር።”

ሐማስ ጥቃት ከመፈጽሙ ጥቂት ወራት በፊት በአካባቢው በተቆጣጣሪነት የሠራችው ኤደን፣ የሐማስ ተዋጊዎች በዋናነት የአካል ብቃት ሥልጠና ሲወስዱ እንደነበር ታስታውሳለች። ከጥቂት ወራት በኋላም የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ወደ “ወታደራዊ ሥልጠና” መቀየሩን ገልጻለች።

በድንበሩ ላይ በሚገኝ በሌላኛው መቆጣጠሪያ ጣቢያ የተመደበችው ጋል [ስሟ ተቀይሯል] ሥልጠናው እየተጠናከረ መሄዱን ታዝባለች።

በድንበር ላይ ያለን አውቶማቲክ የእስራኤል መሣሪያ የሚመስል ሞዴል “ጋዛ እምብርት ላይ” መሠራቱን ከስለላ ፊኛ ባገኘችው ምስል ተመልክታለች።

ጥንካሬውን ለመፈተሽ በሚመስል መልኩ የእስራኤል የብረት ግንብ በመባል በሚታወቀው አጥር አቅራቢያ ቦምቦች እየተቀበሩ ይፈነዱ እንደነበረም በርካታ ሴቶች ገልጸዋል። መስከረም 26 የሐማስ ተዋጊዎች በሞተር ሳይክሎች ድንበሩን ከመጣሳቸው በፊት በአጥሩ አቅራቢያ ትላልቅ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ታይቷል።

አሁን በጦሩ ውስጥ የምታገለግለው እና ቀደም ሲል የቁጥጥር ባለሙያ የነበረችው ሮኒ ሊፍሺትዝ ከጥቃቱ በፊት ካየቻቸው አሳሰቢ ነገሮች አንዱ የሐማስ ተዋጊዎች በመኪና አካባቢውን መቃኘታቸው እና አንዳንዴም ቆም ብለው መመልከታቸው ነው።

 ሮኒ ሊፍሺትዝ
የምስሉ መግለጫ,ሮኒ ሊፍሺትዝ

የሐማስ አባላት “ያወራሉ፣ ወደ ካሜራዎች እና አጥሮቹ ይጠቋቆማሉ፣ አንዳንዴን ፎቶ ያነሳሉ” ስትል ታስታውሳለች።

በአለባበሳቸው ምክንያት የሐማሱ ኑክባ አባል መሆናቸውን መለየት ችላለች። እስራኤል ይህ ቡድን ከመስከረም 26ቱ ጥቃት ጀርባ ካሉት “ዋነኛ ኃይሎች” አንዱ መሆኑን ተናግራለች።

የሮኒ ምስክርነት ቢቢሲ ካነጋገራት ሌላኛዋ የጣቢያው ተቆጣጣሪ ጋር ይመሳሰላል።

አንዳንዶቹ ሴቶችም የወረራ ሙከራዎች እያደጉ መሆኑን ይናገሩ ነበር።

አንዲት ሴት ወታደር ለቢቢሲ ባጋራቻቸው መልዕክቶች ላይ እንደሰፈረው በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ መኪኖች እና የመከላከያ ሠራዊት ወደ እስራኤል ለመሻገር የሚሞክሩ ሰዎችን ያስቆም እንደነበርም ይጠቅሳሉ። ይህ ክስተት እያደገ መጥቶ እንደነበረም ይናገራሉ።

ሴቶቹ በድንበር አካባቢ የባህሪ ለውጦችንም ማየት ጀመሩ።

የጋዛ ገበሬዎች፣ ወፍ አዳኞች እና እረኞች ወደ ድንበሩ አጥር ይበልጥ መቅረብ ጀመሩ ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ከጥቃቱ ቀደም ብለው መረጃ እየሰበሰቡ ነበር ብለውም ያምናሉ።

የድንበር አካባቢ

“ሁሉንም በደንብ እናውቃቸዋለን። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እና ሰዓታቸውን በትክክል እናውቃለን። በድንገት የማናውቃቸውን ወፍ አዳኞችን እና የማናውቃቸውን ገበሬዎች ማየት ጀመርን።

“በፊት ወደ ማይሄዱባቸው ቦታዎች መንቀሳቀስ መጀመራቸውንም አስተዋልን። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ተቀይሯል” ስትል ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገችው አቪጌል ተናግራለች።

ኖአም እንዲሁ ወደ አጥሩ “መጠጋት እና መቅረብ” መጀመራቸውን ታስታውሳለች።

“ገበሬዎቹ ለእርሻ ወደማይመቸው የአጥሩ አካባቢ ይጠጉ ነበር። ስለ አሠራሩ እና እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ መረጃ ከመሰብሰብ ውጪ ምንም ምክንያት የላቸውም። ይህ ለእኛ አጠራጣሪ ነበር” ትላለች።

“ስለ ጉዳዩ ሁልጊዜም እናወራ ነበር።”

ያነጋገርናቸው ሰዎች ሁሉ ስለታዘቡት ነገር አስፈላጊነት የሚያውቁ አልነበሩም።

ሐማስ ሁሌም ጥቃት ለመሰንዘር እያሰለጠነ ነበር።

የድንበር አካባቢ

ከፍተኛ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል ብለው የፈሩ በርካታ የድንበር ተቆጣጣሪዎች ስጋታቸው ሰሚ እንዳላገኘ እንደተሰማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሮኒ በድንበሩ አቅራቢያ ያሉትን መኪኖች ስትመለከት ኃላፊነትዋ ለአዛዣዋ መናገር እና ተሽከርካሪዎቹ ከአካባቢው እስኪርቁ መመልከቷን መቀጠል እንደሆነ ትገልጻለች። ከዚያም በኮምፒዩተር ሪፖርት ታደርጋለች።

እነዚህ ሪፖርቶች የት እንደደረሱ ግን “ምንም አላውቅም” ትላለች።

“ምናልባት ለስለላ ክፍሉ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምን እንደሠሩበት እኔ በትክክል አላውቅም። ሪፖርት ስላደረግነውን እና ስላስተላለፍነው ነገር ማንም መልስ አልሰጠንም” ትላለች።

ኖአ ምን ያህል ጊዜ ሪፖርቶችን እንዳቀረበች ማስታወስ እንደማትችል ትናገራለች። ሁሉም ሰው “ትኩረት ሰጥቶ ሪፖርቱን ቢያስተላልፍም እነሱ [ከክፍሉ ውጭ ያሉ ሰዎች] ምንም አላደረጉም።”

ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ጣቢያው በመጡ ጊዜ እንኳን “ማንም ሰው አያናግረንም ወይም አስተያየታችንን አይጠይቅም ወይም ስለተፈጠረው ነገር ትንሽ አይነግረንም” ስትል አቪጌል ገልጻለች።

“መጥተው ሥራ ሰጥተውን ይሄዳሉ” ትላለች።

“ማንም የማይሰማን ከሆነ እዚህ ምን እንሠራለን?”

ጋል በክፍሏ አዛዥ እንደመሆኗ መጠን በስሯ ካሉ ባልደረቦቿ መረጃ እንደሚደርሷት እና እሷም ይህንኑ ለኃላፊዎቿ ታስተላልፋለች።

ጋል የምታስተላልፈው ሪፖርት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ቢደርስም የተወሰደ እርምጃ የለም።

አብዛኞቹ ሴቶች ብስጭታቸውን እና ጭንቀታቸውን ለቤተሰቦቻቸው እንዳጋሩ ይናገራሉ።

የሻሃፍ እናት የሆነችው ኢላና “ማንም የማይሰማን ከሆነ እዚህ ምን እንሠራለን?” ማለቷን ታስታውሳለች። “ሴቶቹ የተዝረከረከ ነገር እንዳለ እንደሚመለከቱ ነግራኛለች። እኔም ‘እያማረርሽ ነው?’ ብዬ ጠየቅኳት።

“ስለሠራዊቱ በትክክል ባይገባንም ችግሩ ያለው ከበላይ ባሉት ላይ መሆኑን ተረድቻለሁ” ትላለች።

ሻሃፍ ስጋት ቢገባትም ቤተሰቧም እንደሌሎች እስራኤላዊያን ቤተሰቦች ሁሉ በሠራዊቱ እና በእስራኤል መንግሥት ላይ ሙሉ እምነት ነበራቸው። አንድ ነገር ቢታቀድ እንኳን በፍጥነት እንደሚፈታ ጭምር ያምኑ ነበር።

ሻሃፍ (በስተግራ) እና እናቷ
የምስሉ መግለጫ,ሻሃፍ (በስተግራ) እና እናቷ ኢላና

“ከጥቃቱ በፊት በነበሩት ወራትም ታያላችሁ ጦርነት ይኖራል በማለት ደጋግማ ተናግራለች። በማጋነኗ ሳቅንባት” ስትል ኢላና ታስታውሳለች።

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ናሃል ኦዝን ሲያጠቃ መጀመሪያ ላይ ከተገደሉት መካከል አንዷ ሻሃፍ ናት።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደገለፀው 1300 ሰዎች የተገደሉበት እና 240 ያህሉ ታግተው የተወሰዱበት ቀን በእስራኤል ታሪክ እጅግ አስከፊው ቀን ነው።

ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት እስራኤል በጀመረችው የአየር እና የምድር ጥቃት በጋዛ ከ24 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጊዜው ባያውቁትም ጉዳዩ ታትዝፒታኒዮትን ብቻ አልነበረም ያሳሰበው። ሐማስ አንድ ያቀደው ነገር እንዳለ የተረዱት ሴቶቹ ብቻ አልነበሩም።

የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመለክተው የሐማስን ዕቅድ የሚገልጽ ዝርዝር ሪፖርት የእስራኤል ባለሥልጣናት እጅ ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ይህ የሐማስ ምኞት እንጂ ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል በማለት ውድቅ አድርገውታል።

በእስራኤል የስለላ ድርጅት ክፍል ውስጥ ተንታኝ የሆነች ባለሙያ ከተገኘው ዕቅድ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሐማስ ከባድ የሥልጠና ልምምድ ማድረጉን ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከሦስት ወራት በፊት አስጠንቅቃ ነበር። ማስጠንቀቂያዋን ከቁብ የቆጠረው ግን እንዳልነበር ጋዜጣው ዘግቧል።

የቢቢሲ የምርመራ ቡድን እንደተመለከተው ከሆነ በሐማስ እና በሌሎች የታጠቁ ቡድኖች የተካሄዱት ወታደራዊ ልምምዶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በይፋ ተለጥፈዋል።

ካርታ

“ሴቶቹ የሚገባቸውን ትኩረት አላገኙም”

ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ኢታን ዳንጎት “ምልክቶቹ እየታዩ ነበር። ሁሉም ምልክቶች ሲሰበሰቡ ቀደም ብሎ ውሳኔ ለመስጠት እና ይህን ለማስቆም እገዛ ማድረግ ይችሉ ነበር” ብለዋል።

“እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ አልተደረገም።”

እስካሁን ሙሉ ምርመራ ባይደረግም በድነeበር ጠባቂዎቹ የቀረበው ሪፖርት “የሚገባውን ትኩረት አላገኘም” ብለዋል።

“አንዳንድ ጊዜ ከከፍተኛ መኮንኖች በራስ መተማመን ጋር የተያያዘ ነው… ለምሳሌ ‘እሰማሃለሁ ግን ካንተ የበለጠ አውቃለሁ። ልምድ አለኝ። እኔ ከአንተ በላይ ነኝ። ስትራቴጂው አለኝ። እናም የሚባለው ነገር ሊሆን አይችልም’ የሚል ሊሆን ይችላል።”

“ወይም አንዳንድ ጊዜ ትምክህት ሊሆንም ይችላል” ብለዋል።

“በስለላ ሥራ ውስጥ በክብ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠህ መረጃ መሰብሰብ እና ምስሎችን መፍጠር ነው። ከእነዚህ ሰዎች ዘንድ ምን እየተፈጠረ እንዳለ ለማወቅ ከእነሱ ጋር ተቀምጠህ የሚናገሩትን በጥሞና ማዳመጥ አለብህ። እነሱ የሚተነትኑበት መንገድ ምንድን ነው? ማለት ያስፈልጋል።”

የቀድሞ የጋዛ ክፍል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አሚር አቪቪ ለችግሩ የፆታ የበላይነት መንስኤ ነው ብለው ባያምኑም የተቆጣጣሪዎቹን ስጋት ለመፍታት ግን የበለጠ መሠራት እንደነበረበት ይስማማሉ።

“በትክክል ምን እንደተፈጠረ በእርግጠኝነት መናገር አልችልም። የሚጠበቀውን ነገር ግን መናገር እችላለሁ” ይላሉ።

“በድንበር ላይ ያሉ ሰዎች ሥራቸውን ሲሠሩ እና ስጋቶች ሲኖራቸው፣ ስጋቱን ማየት እና መገምገም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ባለሙያዎቹ እነሱ ናቸው። እነሱ ናቸው የሻለቃው እና የብርጌዱ “ ዐይኖች።”

ትልቁ ውድቀት ሐማስን ተከላክለናል የሚለው ግምት ነው። “አዎ እየሰለጠኑ ነው፣ አዎ ዕቅድ አላቸው ነገር ግን ተግባራዊ ለማድረግ አይችሉም” የሚለው አስተሳሰብ ስህተት ነው ይላሉ።

የእስራኤል ጦር ብክስተቱ ዙሪያ ምርመራ ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን፣ ለቢቢሲም “እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ወደፊት የሚታዩ ይሆናል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

የድንበር ተቆጣጣሪዎቹ ሪፖርታቸው ለምን ምላሽ እንዳላገኘ የተለያዩ አስተያየቶች አላቸው። አቪጌል ግን የበርካታዎቹን ያነጋገርናቸው ተቆጣጣሪዎች ሃሳብ ትጋራለች፡ “በሥርዓቱ ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምንገኝ ወታደር ስለሆንን ነው…ስለዚህ ቃላችን ሙያዊ ትንተና እንዳነሰው ይቆጠራል።”

“ሁሉም ሰው እንደ ዐይን (ተቆጣጣሪ) ብቻ ነው የሚያየን። እንደ ወታደር አያዩንም” ትላለች ሮኒ።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሦስት ወራት በኋላም በሕይወት የተረፉት ተቆጣጣሪዎች እና የተገደሉት የተቆጣጣሪዎች ቤተሰቦች ሐዘን ላይ ሆነው ምርመራ እስኪደረግ ድረስ የተፈጠረውን ነገር ለመረዳት እየታገሉ ነው።

በሻይ አሽራም መኝታ ክፍል ውስጥ ወታደራዊ መለዮዎች ተሰቅለዋል። ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሳ የተነሳቻው ፎቶዎች እና ምስሎችም ይገኛሉ።

አባቷ ድሮር አንዳንድ ጊዜ ወደ ክፍሉ ገብቶ እንደሚያለቅስ ይገልጻል።

“ሥራዋን በጣም ትወድ ነበር። ሠራዊቱን ትወደው ስለነበር ወታደር መሆን ትፈለግ ነበር” ይላል።

“የታክሲ ሹፌር በመሆኑ ሰዎችን ከባቡር ጣቢያ እወስዳለሁ። አባት ሴት ወታደር ልጁን መጥቶ ሲቀበል ሳይ በጣም ይጎዳኛል። በጣም እቀናለሁ።”

የሻይ አባት ድሮር
የምስሉ መግለጫ,የሻይ አባት ድሮር

“ሁሉም ቦታ ከእኔ ጋር ነው”

በቤተሰቦቿ ቤት የምትገኘው ኖሃ ጓደኞቿ ሲዘፍኑ እና ሲጨፍሩ የሚያሳዩ የቆዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ቪዲዮዎችን በየቀኑ ትመለከታለች። መኝታ ቤቷ ውስጥ ብቻዋን መሆን ስለሚያስፈራት ሶፋ ላይ መተኛት ጀምራለች።

ያሳለፈችው ሁኔታ “ሁሉም ቦታ ከእኔ ጋር ነው። በቅዠቶች እና ሀሳቦች፣ በእንቅልፍ እጦት እና በምግብ ፍላጎት ማጣት ውስጥም አብሮን ነው። አሁን በፊት የነበርኩት ሰው አይደለሁም” ትላለች።

ከሌሎች ባልደረቦቿ ጋር የተጋራችውን የዋትስአፕ መልዕክት እያየች እና ስማቸውን እየጠራች ይህቺ “ተገድላለች” ወይም “ታግታለች” በማለት ትጠቁማለች።

በናሃል ኦዝ የሚገኘው የመሥሪያ ቦታቸው አሁን ኦና ሆኗል። ሐማስ ለጥቃቱ ሲዘጋጅ ያሳዩዋቸው ስክሪኖች ተቃጥለዋል፣ ወድመዋል።

ሐማስ ወደ ናሃል ኦዝ ሰርጎ በመግባት በርካታ ሰዎችን ሰዎችን ገድሏል።

ከሟቾቹ መካከል ለእስራኤል መንግሥት ድንበሩን በቅርበት የሚከታተሉ እና የእስራኤልን ግዙፍ ኃይል እና አቅም እያወቁም እንደዚህ ያለ ጥቃት አንድ ቀን ሊፈጠር እንደሚችል የሰጉት በርካታ ሴቶች ይገኙባቸዋል።