January 17, 2024 – Konjit Sitotaw 

ጋዜጠኛ ተመስገን “ትክክለኛ ፍትህ አይሰጡኝም” ያላቸውን የጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ጠየቀ

ዛሬ ጥር 7ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለተ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ጉዳይ ከመታየቱ በፊት አቤቱታ አቅርቧል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን በአቤቱታው  “የግራ ዳኛ የሆኑት አቶ መሐመድ አሕመድ ትክክለኛ ፍትሕ ይሰጣሉ ብዬ ስለማላምን በዚህ ጉዳይ ከችሎት እንዲነሱልኝ እንዲነሱልኝ እፈልጋለሁ” ብሏል፡፡
የችሎቱ የመሃል እና የቀኝ ዳኞች ለአፍታ ከተማከሩ በኋላ፣ አቤቱታውን በጽሑፍ እንዲያቀርብ ሲፈቅዱለት፤ ተመሰገን “በእዚህ ችሎት በርካታ ጋዜጠኞች ስላሉ አቤቱታዬን በንባብ እንዳሰማ ሊፈቀድልኝ ይገባል፤” ሲል ጠይቋል፡፡
በዚህም ዳኞቹ ሃሳቡን አሳጥሮ እንዲያቀረብ የፈቀዱ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ተመስገንም በጽሑፍ ያዘጋጀውን አቤቱታ ለችሎቱና ለታዳሚው አንብቧል፡-
አቤቱታውም “ዐቃቤ ሕግ ጥቅምት 1/2015 ዓ.ም ባቀረበው የይግባኝ ቅሬታ 2ኛ ክስን በሚመለከት 3ኛ እና 4ኛ ፍሬ ነገሮች፤ እንዲሁም 3ኛ ክስን የይግባኝ ቅሬታ ያላቀረበበት መሆኑን ጠቅሶ ወደፊት ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ውጤቱን ተመልክቶ የይግባኝ ቅሬታ እንደሚያቀርብበት በይግባኝ ማመልከቻው ላይ በግልጽ አመላክቶ እያለ፣ ታህሳስ 17/2015 ዓ.ም መልስ ሰጪን ‹ያስቀርባል› በሚል ትዕዛዝ ከሰጡት ዳኞች መካከል አቶ መሐመድ አሕመድ የሚገኙበት መሆኑን አረጋግጫለሁ” ይላል፡፡
ተመስገን ይቀጥልና “በችሎቱ የተሰጠው ትዕዛዝም ዐቃቤ ሕግ በ2ኛ ክስ ቅሬታ ያላቀረበባቸውን 3ኛ እና 4ኛ ፍሬ ነገሮችን በመጨመር፤ እንዲሁም 3ኛ ክስን በማካተት ‹በ1ኛ እና 2ኛ ክሶች መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ እንዲሰናበት፣ 3ኛ ክስን በሚመለከት ክስ የቀረበበት ድንጋጌ ወደ ጥላቻ ንግግር ወይም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከለከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 በመለወጥ እንዲከላከል በአብላጫ ድምጽ የተሰጠውን ብይን፤ እንዲሁም የተጠቀሰውን አዋጅ ለጉዳዩ ያለውን አግባብነት መጣራት ያለበት መሆኑን ስለታመነበት መልስ ሰጪ ‹ይቅረብ› ብለናል በሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡” ሲልም ያክላል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ለችሎቱ እንዳመለከተው፣ ይህ ትዕዛዝ ዐቃቤ ሕግ በይግባኝ አቤቱታው ከጠየቀው ዳኝነት በማለፍ የተሰጠ እንደሆነ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
ተመስገን ሃሳቡን ቀጥሎ ፤ “ዳኛ መሀመድ በዚህ ጉዳይ ከችሎት ሳይነሱ ‹ይቀጥሉ› ቢባል፣ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እንደመሆኑ መጠን በመዝገቡ ላይ ትክክለኛ ፍትሕ ይሰጣሉ ብዬ የማላምን እና ወደፊትም የሚሰጠው ፍርድ ነፃና ገለልተኛ ይሆናል ብዬ ስለማላምን በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 33/1/ሠ/ መሠረት የግራ ዳኛ የሆኑት አቶ መሐመድ አሕመድ በዚህ ጉዳይ ከችሎቱ እንዲነሱልኝ እጠይቃለሁ፤” ሲል አቤቱታውን ደምድሟል፡፡
የጋዜጠኛውን አቤቱታ ያዳመጠው ችሎቱም “ዳኛው ይነሱ ወይም አይነሱ” የሚለውን ለመወሰን እና በዋናው ክስ ላይ ጋዜጠኛው የሚያቀርበውን መልስ ለመቀበል ለጥር 28/2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡