January 17, 2024 – Konjit Sitotaw 

በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ዋና ከተማ ዙሪያ ዛሬ ጧት በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለተወሰነ ሰዓታት የቆዬ በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች፣ ተኩስ የተከፈተው የፋኖ ታጣቂዎች በተለያዬ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ በመጠጋታቸው ሳይኾን እንዳልቀረ ተናግረዋል።

አንድ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኛ፣ እሳቸውን ጨምሮ የፋብሪካው ሠራተኞች በጧት ወደ ሥራ ገብተው እንደነበር ገልጠው፣ በከተማዋ አጠገብ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ስንሰማ ከሥራ ወጥተናል ብለዋል።

ይህ ዘገባ እየተጠናቀረ ባለበት ዛሬ እኩለ ቀን ላይ የተኩስ ልውውጥ ባይኖርም፣ በከተማዋ እንቅስቃሴ አለመኖሩንና የመንግሥትና የግል ተቋማት ዝግ መኾናቸውን ዋዜማ ተገንዝባለች።

ነዋሪዎቹ፣ በተኩስ ልውውጡ በከባድ መሳሪያ የተመቱ መኖሪያ ቤቶችና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለጊዜው በትክክል እንደማያውቁ ገልጸዋል።