January 17, 2024 – Konjit Sitotaw
ኢትዮጵያዊያን የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት የዲጂታል መታወቂያን ለመያዝ ሊገደዱ እንደኾነ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ዳይሬክተር ዮዳሔ ዘሚካኤል ለአገር ወስጥ የዜና ምንጮች ተናግረዋል።
በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኩል በተለያዩ ምዕራፎች ይተገበራል ከተባለው የምዘገባ ሂደት በኋላ፣ ዲጂታል መታወቂያ ያልያዙ ዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ከማግኘት እንደሚታገዱ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል ተብሏል።
“ኹሉንም አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል መታወቂያ የማካተት ዕቅድ አለን” ያሉት ዮዳሔ፣ “ይኽም የአዋጁ ራዕይ ነው” ማለታቸው ተዘግቧል።
ዳይሬክተሩ፣ ተቋማት ዲጂታል መታወቂያ ያልያዙ ደንበኞቻቸውን አገልግሎት የመንፈግ ሕጋዊነት አላቸው ማለታቸውም ተገልጧል።
እስከ አኹን አገልግሎቱን ለማግኘት አራት ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ሲመዘገቡ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2025 መታወቂያ ለማግኘት ዕድሜያቸው የሚፈቅድላቸውን ኹሉንም ዜጎች ለመመዝገብ ተይዞ የነበረው ቀነ-ገደብ ወደ 2028 ሊገፋ መቻሉም ተጠቅሷል።