
17 ጥር 2024, 15:18 EAT
ኤኤንኤ የተሰኘው አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በአንድ ሰካራም መንገደኛ ምክንያት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚያደርገውን ጉዞ አቋርጦ ወደ ጃፓን ተመልሷል።
“በጣም ሰክሮ ነበር” የተባለው የ55 ዓመቱ አሜሪካዊ መንገደኛ አንድ የበረራ አስተናጋጅን ነክሷል።
የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት መንገደኛው የአስተናጇን ክርን ነው የነከሰው።
የጃፓን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግለሰቡ የእንቅልፍ መድኃኒት ወስጄ ስለነበር የተፈጠረውን አላስታውስም ሲል ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሰል ክስተቶ ከወደ ጃፓን መሰማታቸው የተለመደ ሆኗል።
159 መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው አውሮፕላን ግለሰቡ መረበሽ ሲጀምር ፓሲፊክ ውቅያኖስን እየተሻገረ ነበር።
ከክስተቱ በኋላ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ጉዟቸውን አቋርጠው ወደ ጃፓን ሀኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ ተመልሰዋል።
አየር መንገዱ እንደገለጠው አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ግለሰቡ ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል።
- ወደ ሃርጌሳ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አውሮፕላን በሶማሊያ መንግሥት እንዲመለስ ተደረገ17 ጥር 2024
- የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ለማን ይሰጣል? በኢትዮጵያስ ማግኘት ይቻላል?17 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ አዲስ የታጠቀቻቸው ጄት እና ድሮን አቅማቸው ምን ያህል ነው?17 ጥር 2024
ኤኤንኤ አየር መንገድ በመሰል ያልተጠበቀ ክስተት ጉዞው ሲስተጓጎልበት በቅርብ ቀናት ይህ ሁለተኛው ነው። የጃፓን አቪየሽን ደግሞ በቅርብ ጊዜያት ብቻ አምስት ጊዜ የዜና ምንጭ ሆኗል።
ባለፈው ቅዳሜ የኤኤንኤ ንብረት የሆው አውሮፕላን መስኮት መሰንጠቁን ተከትሎ በረራው ወደ መነሻው ለመመለስ ተገዷል።
ስንጣቂው የታየው የአብራሪዎቹ ጋቢና [ኮክፒት] ውጫዊ ክፍል ላይ ቢሆንም የደረሰ ጉዳት ግን አልነበረም።
አየር መንገዱ በመስኮቱ መሰንጠቅ ምክንያት ምንም ዓይነት ችግር አልፈተጠረም ሲል በቃለ አቀባዩ በኩል መናገሩ ይታወሳል።
ከሁሉ የከፋ ሆኖ የተመዘገበው የሰሞኑ ክስተት ግን ይህ አይደለም።
በአውሮፓውያኑ ጥር 2 በአዲሱ ዓመቱ ማግስት አንድ የጃፓን አየር መንገድ አውሮፕላን ከድንበር ጠባቂ አነስተኛ አውሮፕላን ጋር ተጋጭቷል።
አውሮፕላን በእሣት ተያይዞ ከመጋየቱ በፊት 379 ተሳፋሪዎች እንዲወጡ ተደርጓል።
ነገር ግን በአነስተኛው አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩ ስድስት ሰዎች መካከል አምስቱ ሕይወታቸው አልፏል።
አነስተኛው አውሮፕላን በጃፓን የተከሰተውን ርዕደ መሬት ተከትሎ የእርዳታ ሥራ ማከናወን ላይ ነበር።
ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ በጃፓኗ ሆካይዶ ደሴት የኮሪያ ኤር ንብረት የሆነ አውሮፕላን ከካቲ ፓሲፊክ አውሮፕላን ጋር ክንፋቸው ተገጫጭቶ እንደነበር ተሰምቷል። በክስተቱ የተጎዳ ሰው የለም።
በተመሳሳይ ባለፈው እሑድ የኤኤንኤ አውሮፕላን እና የደልታ አውሮፕላን በቺካጎ አውሮፕላን ማረፊያ ተጋጭተዋል። ነገር ግን ግጭቱ አነስተኛ ስለሆነ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም።