
17 ጥር 2024, 18:18 EAT
አንዲት ጀርመናዊት በመልክ የምትመስላትን አምሳያዋን በመግደል እራሷ እንደሞተች ለማስመሰል ሞክራለች ተብላ ተከሳለች።
ጉዳዩ በእንግሊዝኛ “ዶፕልንጋንገድ መርደር” የተሰኘ ስም ተሰጥቶታል። ዶፕልጋንገር በግርድፍ ትርጉሙ ቁርጥ ተመሳሳይ መልክ ያለው ማለት ነው።
የ24 ዓመቷ ሻራባን ኬ እና ተባባሪዋ የሆነው የ25 ዓመት ግለሰብ በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ችሎት ፊት ቀርበዋል።
ዓላማቸው የነበረው ሻራባንን የምትመስል ሴት ፈልገው በመግደል ሻራባን እንደሞተች ማስመል ነበር ተብሏል።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ተጠርጣሪዋ ዕቅዷ መሰሏን ከገደለች በኋላ እሷ የሞተች በማስመሰል አዲስ ሕይወት መጀመር ነበር።
ነገር ግን ግድያውን በፈፀመች በሁለተኛው ቀን የፖሊስ ካቴና ሲሳይ ሆናለች።
እሷ እና ተባባሪዋ ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ ወንጀሉን አልፈፀምንም ሲሉ ክደዋል።
የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚያሳዩት ጀርመናዊት አራቃዊቷ ሻራባን ኬ የተጠረጠችበትን ወንጀል የፈፀመችው ነሐሴ 2022 (እአአ) ነው።
እሷን የሚመስሉ ሴቶችን ኢንስታግራም ላይ አጥምዳ በአካል ታገኛቸው እንደነበር የምርመራ መዛግብቱ ጠቁመዋል።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ሟች የ23 ዓመቷ አልጄሪያዊት ኻዲጃ ኦ ናት።
- ወደ ሃርጌሳ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አውሮፕላን በሶማሊያ መንግሥት እንዲመለስ ተደረገ17 ጥር 2024
- ታካሚዎች ያለ ልክ እንዲወፍሩ የሚገፋፋው የሰውነት ቅነሳ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ16 ጥር 2024
- ‘ሰካራም መንገደኛ’ የበረራ አስተናጋጅ በመናከሱ አንድ አውሮፕላን ጉዞውን አቋርጦ ወደ ጃፓን ተመለሰ17 ጥር 2024
ኻዲጃ በአንድ የውበት ሳሎን ውስጥ በነፃ አገልግሎት እንደሚሰጣት ተነግሯት ነበር ወደ ሥፍራው ያቀናችው።
በደቡባዊ ጀርመን ከምትገኝ አንዲት ከተማ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ይዘዋት ወደ ባቫሪያ እንደወሰዷት ክሳቸው ያሳያል።
ሟች በሻራባን ኬ ጥቁር ሜርሴዲስ መኪና ውስጥ 56 ጊዜ በጩቤ ተወግታ እንዲሁም ጭንቅላቷ ተመትቶ መንገድ ላይ ተጥላ ተገኝታለች ይላል የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ።
የሟች ሬሳ በተገኘበት ወቅት መጀመሪያ ታስቦ የነበረው ሻራባን ኬ እንደሞተች ለማስመሰል ነበር።
ነገር ግን ሁለቱ ተጠርጣሪዎች አንድ ፒዛ ቤት ተቀምጠው ሳለ በመታየታቸው በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የሻራባን ቤተሰቦች የመጡት ሰሜን ኢራቅ ከሚገኘው የያዝዲ ማኅበረሰብ እንደሆነ የዘገቡት የጀመርን መገናኛ ብዙኃን፣ የትዳር ሕይወቷ አለመሳካቱ ወንጀል ለመፈፀም አነስቷት ሊሆን ይችላል ሲሉ ፅፈዋል።
ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎች ከሰበሰበ እና የዐይን እማኞችን እንዲሁም የፅሑፍ መልዕክቶችን ከተመለከተ በኋላ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ክስ መሥርቷል።
ሁለቱ ግለሰቦች ከዚህ በተጨማሪ የሻራባንን የቀድሞ ባል ወንድም ለማስገደል ገዳይ ቀጥረዋል ተብለው ተከሰዋል።
ነገር ግን ግድያውን ለመፈፀም 5 ሺህ ዩሮ የተቀበለው ግለሰብ ድርጊቱን እንዳልፈፀመ ተዘግቧል።
አልፎም ወንዱ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር እያለ የዐይን እማኞችን እንዲገድልለት ሌላ ታሳሪ ለማሳመን ሞክሯል ተብሎም ተከሷል።
የሁለቱ ተጠርጣሪዎች የችሎት ሂደት ማክሰኞ ዕለት የጀመረው ዘግይቶ ነው።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ዐቃቤ ሕግ በቅርቡ ተጨማሪ መዝገብ ስላመጣ እሱን ሳንመርምር የሚጀመር ችሎት ፍትሐዊ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።
ነገር ግን ችሎቱ ከክስ በኋላ ተጨማሪ መዝገብ መቅረቡ አዲስ ነገር አይደለም ሲል የጠበቃዎቹን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።
ችሎቱ በሚቀጥለው ሳምንት ድጋሚ ጉዳዩን ለመመልከት ቀጠሮ ይዞ ተበትኗል።